ላለፉት ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ የነበረው ተከላካይ ማረፊያው ታውቋል።
ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ አዲስ ክለብ መቀላቀሉ ተረጋግጧል። ትውልድ እና ዕድገቱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ውስጥ በምትገኝ አረብ ሰፈር ተብላ በምትጠራ መንደር የሆነው ይህ ተጫዋች ቤኒሻንጉልን ወክሎ በተለያየ የፕሮጀክት ውድድር ላይ ሲሳተፍ ከቆየ በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን እንዲሁም በብሔራዊ ሊጉ ንስር ቆይታ አድርጎ ከ2011 አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተጫውቷል።
ከዚህ ቀደም በስሑል ሽረ፣ ወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ሁለት ድንቅ ዓመታት አሳልፎ አንድ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳበትን ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው የግራ መስመር ተከላካዩ አሁን ደግሞ በአንድ ዓመት ውል ኢትዮጵያ መድንን ተቀላቅሏል። ቀደም ብለው ጋቶች ፓኖምን የግላቸው ያደረጉት መድኖች ያሬድ ካሳዬን በረዥም ጊዜ በጉዳት ማጣታቸው የሚታወስ ሲሆን አዲሱ ፈራሚ ረመዳን የሱፍም የሱን ቦታ ተክቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ የሊግን ክብር ካነሱት የቀድሞ ቡድን አጋሮቹ ሀይደር ሸረፋ፣ ዳዊት ተፈራ እና ጋቶች ፓኖም ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል።