አፈወርቅ ኃይሉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመልሷል።
በርከት ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ ወጣት ተጫዋቾችን በማዘዋወር ቡድናቸውን በማጠናከር ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አማካዩ አፈወርቅ ኃይሉን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል። ከዚህ ቀደም በድሬ ፖሊስ ጨምሮ ወልዋሎ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ባህርዳር ከተማ እንዲሁም ዋናው እና የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድንን ማገልገል የቻለው አማካዩ ላለፉት ሳምንታት ከፈረሰኞቹ ጋር ልምምድ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ቡድኑን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል። ወልዋሎን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ ከተጫወቱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አፈወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመቀላቀል ከተስማማ በኋላ ዛሬ ጥዋት የህክምና ምርመራውን ያጠናቀቀ ሲሆን በዛሬው ዕለት ዝውውሩን ያገባድዳል ተብሎም ይጠበቃል።
ሦስት ጨዋታዎችን አካሂደው በሦስት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሊጉ ከአህጉራዊ ጨዋታዎች ሲመለስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚገጥሙ ይሆናል።