የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል።
ወደ ፕሪምየር ሊጉ በተመለሱበት ዓመት እስከ አሁን ሦስት ጨዋታዎችን አድርገው አንድ ሽንፈት ሁለት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሁለት አማካዮችን ሜዲካል አጠናቀው ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።
አበባየሁ ዮሐንስ የመጀመሪያው ፈራሚ ሆኖ ክለቡን ተቀላቅሏል። የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ ስልጤ ወራቤ እና ሀድያ ሆሳዕና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ወደ ሲዳማ ቡና ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ ቆይታ ካደረገበት ክለብ ጋር ከቀናቶች በፊት ቀሪ የውል ዘመን እያለው በጋራ ስምምነት ከተለያየ በኋላ ቀጣይ ማረፊያውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ አድርጓል።
ሌላኛው ፈራሚ አማካዩ አባይነህ ፌኖ ሆኗል። ከዚህ ቀደም በኢኮስኮ ፣ በሀዋሳ ከተማ ፣ በወልቂጤ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫውቶ ያሳለፈው አማካዩ በባህርዳር ከተማ ካደረገው የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ኤሌክትሪክን በይፋ ተቀላቅሏል።