ቢጫ ለባሾቹ ተከላካይ ለማስፈረም ተስማምተዋል

በፕሪምየር ሊጉ አጀማመራቸው ያላማረላቸው ወልዋሎ አዲግራቶች የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የግላቸው ለማድረግ ከጫፍ ደርሰዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተመለሱበት ዓመት ካደረጓቸው ሦስት የሊጉ ጨዋታዎች አንድም ነጥብ መያዝ ያልቻሉት በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲዎች ያለፉት ሁለት ቀናት ጋናዊውን ተከላካይ ሠለሞን አዶማኮን እንዲሁም አማካዮቹ ዮናስ ገረመው እና ሳምሶን ጥላሁንን ያስፈረሙ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነውን የአብስራ ሙሉጌታን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ከስምምነት መድረሳቸው ታውቋል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ መነሻውን ካደረገ በኋላ በማስከተል ለጅማ አባጅፋር ፣ መቻል እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በሻሸመኔ ያሳለፈው የመሐል ተከላካዩ ከወራት በፊት ወደ ቀደመ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመልሰውን ዝውውር በስምምነት ደረጃ አገባዶ የነበረ ቢሆን ከክለቡ ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ከተለያየ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻውን ወልዋሎ አድርጓል።