ላለፉት ዓመታት በቡናማዎቹ በለት ቆይታ የነበረው አማካይ አዲሱ የፈረሰኞቹ ተጫዋች ሆኗል።
በትናንትናው ዕለት የቀድሞ የወልዋሎ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ አማካይ አፈወርቅ ኃይሉ እንዲሁም ኮትዴቭዋራዊው አጥቂ መሐመድ ላሚን ኮኔ ለማስፈረም መስማማታቸውን የዘገብነው ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁን ደግሞ ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ቆይታ የነበረው አብዱልሃፊዝ ቶፊቅን ማስፈረማቸው ታውቋል። የበርካታ ወጣት ተጫዋቾች መነሻ ከነበረው የደደቢት ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ በ2011 የውድድር ዓመት የመጨረሻ ሳምንታት በተሰጠው የመሰለፍ ዕድል ከእግር ኳስ ቤተሰቡ ጋር የተዋወቀው ወጣቱ አማካይ በ2012 እናት ክለቡን ለቆ በሰበታ ከተማ ለሁለት ዓመታት እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ከተጫወተ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል።
ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለው አማካዩ ወደ ፈረሰኞቹ የሚያደርገው ዝውውር በመሀል እክል ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን ዝውውሩ እውን ሆኗል።