የዋልያዎቹን ስብስብ ሁለት ተጫዋቾች ተቀላቅለዋል

አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ለተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዝግጅቱን በትናትናው ዕለት የጀመረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ሁለተኛ ቀን ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል በአሜሪካ ከሚገኘው ሱራፌል ዳኛቸው በቀር 22 ተጫዋቾች የተገኙ ሲሆን አሁን ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች ቡድኑን መቀላቀላቸው ታውቋል።

ቡድኑን የተቀላቀሉት የሱሁል ሽረ ተጫዋቾች የሆኑት አማካዩ ጃዕፈር ሙደሲር እና አጥቂው ፋሲል አስማማው ናቸው።

ሁለቱም ተጫዋቾች ስሁል ሽረ በሊጉ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ባሳዮት መልካም እንቅስቃሴ መነሻነት ብሔራዊው ቡድን መቀላቀላቸው ሲታወቅ በዛሬው የብሔራዊ ቡድኑ ልምምድ ወቅት በመገኘት ዝግጅት መጀመራቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታውን ጥቅምት 2 እና 5 ቀን ከጊኒ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።