ወልዋሎዎች ተጨማሪ ተጫዋች ለማስፈረም ተስማምተዋል

ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ንብ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው የፊት መስመር ተሰላፊ ቢጫዎቹን ለመቀላቀል ተስማምቷል።


በፕሪምየር ሊጉ መልካም አጀማመር ያላደረጉት እና ባለፉት ቀናት ቡድናቸውን ለማጠናከር ጋናዊው ሰለሞን አዶማኮን ጨምሮን የዓብስራ ሙልጌታ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ዮናስ ገረመውን ያስፈረሙት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ የፊት መስመር ተጫዋቹ ናትናኤል ሰለሞንን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን ወክሎ በሴካፋ ዞን የአፍሪካ ከሀያ ዓመት በታች ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ለመሳተፍ በታንዛንያ የሚገኘው እና ከመቻል ወጣት ቡድን ተገኝቶ ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ንብ ድንቅ ብቃት ያሳየው ተስፈኛው ተጫዋች ከውድድሩ መልስ በይፋ የወልዋሎ ተጫዋች ለመሆን ከስምምነት ደርሷል።

ባከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት ወልዋሎዎች በቀጣይ መቻል፣ ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚገጥሙ ይሆናል።