ሴካፋ U20 | ጉማሬዎቹ ቀይ ቀበሮዎቹን ረተዋል


በ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የምድብ ሁለት ጨዋታ ኢትዮጵያ በዩጋንዳ 3ለ0 በመሸነፍ ውድድሯን ጀምራለች።

12፡00 ሲል አዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ላይ በሩዋንዳዊው ዳኛ ሩሪሳ ፊዴሌ በተመራው ጨዋታ ኢትዮጵያ በኳስ ቁጥጥሩ በተለይ ከኋላ በሚደረጉ ቅብብሎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በይበልጥ ወደ ግራ መስመር ተሰላፊው አብዱሰላም የሱፍ በኩል የማጥቂያ መነሻቸውን በማድረግ ብልጫውን መያዝ ቢችሉም በቅብብል ወቅት የሚፈጠሩ ስህተቶችን በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም የሚጥሩት ዩጋንዳዎች ግን የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አኳያ ፍፁማዊ ብልጫን ወስደዋል።

 

17ኛው ደቂቃ ላይ አላን ኦይርወዝ ከሳጥን ውጪ ካደረጋት ሙከራ በኋላ በድግግሞሽ ለዋልያዎቹ ተከላካዮች ፈተና መሆን የቻሉት ዩጋንዳዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ሪቻርድ ኦኬሎ ከቀኝ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ደግፌ አለሙ በተሳሳተ አቅጣጫ ገጭቶ ያቀበለውን ጎድፍሬይ ሴኪቤንጎ በድንቅ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አንተነህ ተፈራ በመልሶ ማጥቃት ለኢትዮጵያ ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ከተባለችዋ አጋጣሚ በኋላ ባሉት ቀሪዎቹ ደቂቃዎች በይበልጥ ጉማሬዎቹ ጫናን እያሳደሩ በፈጣን ሽግግሮች አከታትለው ሙከራዎችን ሰንዝረዋል።

በ28ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል ጆን ዴንቤ ከዋንጫ ቱት ጋር ታግሎ የመታውን ኳስ አብዩ የመከተበት እና ጎድፍሬይ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ በግሩም መቀስ ምት ሞክሯት የግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት የመለሰበት ተጠቃሾቹ ሙከራዎች ናቸው። በቀጣዮቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የተጋጣሚን የማጥቃት ሽግግር መቋቋም እየከበደው የመጣው የአሰልጣኝ ስዩም ከበደው ቡድን ከደረሰበት ተደጋጋሚ ጥቃቶች በኋላ ማለትም 40ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ አለን ገጭቷት ስትመለስ ሞፓሳ ስዋቢሪ የኢትዮጵያ የተከላካይ ክፍል ተጫዋቾች ድክመት ታክሎበት ሁለተኛ ጎል አድርጓት ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው እና ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ አቀራረብ ባልተስተዋለበት ጨዋታ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የቁጥጥር ድርሻውን አሁንም ቀይ ቀበሮዎቹ መያዝ ቢችሉም ረጃጅም በሆኑ ኳሶቻቸው በቶሎ ሦሰተኛው የሜዳ ክፍል የሚደርሱት ጉማሬዎቹ የማጥቃት ደመነፍሳቸው ግን ከፍ ያለ ነበር።

ያሬድ ብሩክ እንዲሁም ግሩም ሀጎስ ከቅጣት ምት ካደረጓቸው ያልተሳኩ ሙከራዎች ውጪ በቀላሉ ለተጋጣሚያቸው እጅ እየሰጡ የቀጠሉት ኢትዮጵያዎች አቡባካሊ ዋሉሲንቢ እና ጆን ዴንቤ አከታትለው ከሰነዘሯው ሙከራዎች በኋላ ጨዋታው ብዙም አጋጣሚዎች ሳይፈጠሩበት ብዙ ደቂቃዎችን ተጉዞ ሊጠናቀቅ 90ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ኪሶሎ ኢኖሰንት በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታት ኳስ በተከላካይ ተጨርፋ የግብ ዘቡ አብዩ ካሳዬ መረብ ላይ አርፋ በመጨረሻም ጨዋታው በዩጋንዳ 3ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።