አፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው የፌዴሬሽኑ 16ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል።
በ2014 በተካሄደው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ወቅት ፌዴሬሽኑን ለአራት ዓመታት የሚመሩ ስራ አስፈፃሚዎችን ለመምረጥ ምርጫ ሲካሄድ የሱማሌ ክልልን በመወከል ወ/ሮ ፋይዛ ራሺድ ስራ አስፈፃሚ በመሆን መመረጣቸው ይታወቃል።
ያለፉትን ዓመታት በአንዳንድ ስራዎች ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት ስራ አስፈፃሚዋ አሁን የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ዛሬ እየተካሄደ ባለው 16 ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፕሬዝደንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አሳውቀዋል።
“የሱማሌ ክልል የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል የነበሩት ወ/ሮ ፋይዛ ራሺድ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል ይህን ተከትሎ ለጉባኤው የማቅረብ ደንቡ ስለሚያስገድድ በእርሳቸው ምትክ ሌላ ለመተካት ስለሚገባ ምን መደረግ አለበት” በማለት ፕሬዝደንቱ በመድረኩ ሀሳብ እንዲሰጥበት ካደረጉ በኋላ በቀጣይ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ አልያም ስራ አስፈፃሚው አስመራጭ ኮሚቴው ጋር ተነጋግሮ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት የሱማሌ ክልል ተወካይ እንደሚተካ ተገልጿል።
ክቡር ፕሬዝደንቱ ወ/ሮ ፋይዛ ራሺድ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን እንጂ በምን ምክንያት ከስራ አስፈፃሚ አባልነት ራሳቸውን ለማግለል እንደፈለጉ ከመድረኩ የተገለፃ ነገር ባይኖርም በዛሬው መድረክ ላይ በአካል ተገኝተው መልቂያቸውን በይፋ ለጉባኤው እንዲያቀርቡ የተደረገው ጥረት በእርሳቸው አለመገኘት አለመሳካቱ ተመላክቷል
በሌላ ዜና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዲስ አባል ሆኑ መፅደቁ ተረጋግጧል።