መቶ ዓለቃ ፍቃደ ማሞ በሀገራችን ስታዲየሞች አሁናዊ ሁኔታ ዙርያ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 16ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እያካሄደ ይገኛል ፤ በመድረኩ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዝደንት እና የፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማህበሩ ፕሬዝደንቱ መቶ ዓለቃ ፍቃደ ማሞ በስታዲየሞቻችን ግንባታ እና አሁናዊ ሁኔታ ዙርያ ጠንከር ሀሳቦችን በመድረኩ አንስተዋል።


“ የሜዳዎች ጉዳይ ተድበስብሶ መቆየቱ ቅር ይለኛል” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት መቶ ዓለቃ ፈቃደ ንግግራቸው ሲቀጥሉ “እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ስታዲየም በኮቪድ እና በእድሳት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ካቆመ ከአራት ዓመት በላይ ሆኖታል በዚህ ምክንያት በብሔራዊ ቡድናችን ላይ በገንዘብ የማይቆጠር የሀገርን ድጋፍ እንዳያገኝ ከፍተኛ ኪሳራ አጋጥሞት ከሀገር ወጥቶ ለመጫወት ተገዷል። ክለቦችም በተለይ የአዲስ አበባ ክለቦች ያስከተለው ጣጣ በርካታ ነው። ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ሆኗል” ያሉ ሲሆን “በጦርነት ምክንያት የመቐለን ስታዲየም አጥተናል መቼ ሜዳው ለውድድር ዝግጁ ይሆናል የሚለው መልስ የሚፈልግ ጉዳይ ነው።  የባህርዳር ስታዲየምም ቢሆን በአካባቢው ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በእድሳት ላይ በመሆን ይህ ሜዳ አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኗል። የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየምም በተለያዩ ጉዳዮች በተለይም ከደቡብ ክልል ወደ ሲዳማ ክልል በተደረገው የክልል ለውጥ ርክክብ ይደረጋል እየተባለ ይኸው ባለቤት አጥቶ ውድድር ማድረግ ካቆመ ሰነባብቷል በዚህም ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰበት ስታዲየም አገልግሎት ባለመስጠቱ ማነው የሚጠየቀው።”ብለዋል።


መቶ ዓለቃ ፈቃደ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ “የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታው ከመጀመሩ በፊት ምክረ ሀሳብ ሰጥተን ነበር ከሳር ተከላ ጀምሮ በተለያዩ ስራዎች ዙርያ የሰጠነው ሀሳብ ተቀባይነት በማጣቱ ከፍተኛ ኪሳራ ተከስቷል። ለዚህ ማነው ተጠያቂ የሚሆነው ሲመከሩም አይሰሙሙ በሀገር ላይ የሞራል፣ የገንዘብ ኪሳራ አስከትሏል ችግሩን በፍጥነት ለማረም ለማስተካከል ፍላጎት የለም ባዶ ቋንቋ ነው የምናወራው እዚህ መድረክ ላይ ክቡር አምባሳደሩ መስፍን ቸርነት አሉ መልስ ሊሰጡን ይገባል ብለዋል።”

በመጨረሻም መቶአለቃ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ በከተማው የሚሰራውን የልማት ስራ አያለው ለሌሎች ልማቶች ላይ እንዳለው ፍጥነት እንዴት አንድ ስታዲየም መገንባት አንችልም ከተማዋ ውስጥ የተለያዮ መንግስታት የሚመሯት ነው የሚመስለው።”በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል።