ዋልያዎች በነገው ዕለት ተጋጣሚያቸውን ያውቃሉ

2024 የአፍሪካ ሀገራት ሻምፕዮና የማጣርያ ጨዋታዎች ድልድል በነገው ዕለት ይፋ ይሆናል።


ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ በጋራ ለሚያዘጋጁት የ2024 የአፍሪካ ሀገራት ሻምፕዮና የማጣርያ ጨዋታዎች ድልድል በነገው ዕለት ይፋ የሚደረግ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በነገው ዕለት ተጋጣሚውን የሚያውቅ ይሆናል።

ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 2017 በሦስቱ ጎረቤት ሀገራት ለሚካሄደው ውድድር የሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ያካተተ የሁለት ዙር የማጣርያ ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆኑ የመጀመርያው ዙር የማጣርያ ጨዋታ በጥቅምት ወር ከ15 እስከ 17 ባሉት ቀናት የሚከናወን ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከጥቅምት 22 እስከ 24 ባሉት ቀናት ይከናወናል።

ብሄራዊ ቡድናችን የመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ የሚሻገር ከሆነ ደግሞ የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ ከታህሳስ 11 እስከ 13 ባሉት ቀናት አከናውኖ የመልሱን ጨዋታ ከታህሳስ 18 እስከ 20 ባሉት ቀናት ይከውናል።

ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ ሰባት ውድድሮች በሦስቱ መሳተፍ የቻለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአልጄርያ አስተናጋጅነት ከተካሄደው የ2023 ውድድር በኋላ በተከታታይ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ማጣርያውን ያከናውናል።