አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

👉 “እኔም ጋር ሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስህተት የለም።”

👉 “በቀጣይም ከዚህ በኋላ ሁለት ቡድን ማሰልጠን አልችልም። ፍላጎቱም አይኖረኝም  ምክንያቱም አስቸጋሪ ስለሚሆን ማለት ነው።”

👉 “በቀጣይ በሀሰተኛ 9 ቁጥር ሳይሆን በሙሉ አጥቂ ነው የምንጫወተው።”

👉 “ያለን ዕድል ማሸነፍ ነው። ሌላ ዕድል አይኖረንም።”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እያደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ዛሬ 9 ሰዓት ላይ መግለጫ ተሰጥቷል።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ስለመረጧቸው ተጫዋቾች መጠን ገለጻ በማድረግ ንግግራቸውን በመጀመር ለሃያ ሦስት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል። ከእነዛ ውስጥ ሃያዎቹ ቀድመው እንደገቡ በመጠቆም ሦስት ከውጭ የሚመጡ ተጫዋቾች እንዳሉ ያስረዱት አሰልጣኙ ሁለቱ ዘግየት እንዳሉ እንዳሉ እና ሱራፈል ዳኛቸውም ዛሬ ገና እንደገባ አሳውቀዋል። ሁለት ተጫዋቾችን ጨምረን ነበር ግን ዛሬ ሁለት ቀንሰን ሄያ ሶስት ተጫዋችን ይዘን ነገ ጠዋት እንሄዳለን ያሉት አሰልጣኝ ገብረመድኅን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ዛሬ የመጨረሻ ልምምድ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል።

በመቀጠል ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍም ላለማለፍም ሁለቱ ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው እና ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር ጠንካራ ፉክክር ታደርጋላችሁ ወይ…?

”በሁለት ቀን ልዩነት ነው ጨዋታውን የምናደርገው እኔም እስከማውቀው ቅዳሜና ሰኞ ነው። የአንድ ቀን እረፍት ነው የሚኖረው። በዚህ ሁለት ጨዋታ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመግባታችን ጉዳይ የሚወሰን ይሆናል። በድምር ውጤት የምናገኘው ተስፋ ሰጪ ነው አይደለም የሚለውን ነገር በዛው ጨዋታ ላይ ነው የምናየው። በዚህ በድምር የምናገኘው በተለይ ተጋጣሚያችንን ጥሎ ከማለፍ አንፃር ጥሩ ጠቀሜታ ስላለው የግድ የምንሄደው ለማሸነፍ ነው። ያለን ዕድል ማሸነፍ ነው። ሌላ ዕድል አይኖረንም። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ የሚቀሩ ጨዋታዎች ሁለት ናቸው። ስለዚህ በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ እኛ የምናገኘው ታንዛኒያን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎን ነው። ስለዚህ ከባድ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን። በእርግጥ በሜዳችን ብንጫወት ኖሮ ታንዛኒያን በሜዳችን እናገኛለን ብለን እናስብ ነበር ነገር ግን አሁን አናገኝም ስለዚህ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ስለዚህ አሁን ይሄንን ሁለት ጨዋታ በተመሳሳይ ሀገር ነው የምንጫወተው ምናልባት ከተማው ሊቀያየር ይችላል ግን ዞሮ ዞሮ ለሁለታችንም አንድ ነው። እነሱ ከሜዳቸው ውጪ ነው እኛም ከሜዳችን ውጪ ነው የምንጫወተው እና በዚህ በድምር ውጤት የምናገኘው ውጤት ያው ሊያሳልፈንም ሊጥለንም ስለሚችል ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ያለንን አቅም አሟጥተን ተጫውተን አሸንፈን ያው ተስፋችንን ብራይት ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን።”

ስለሚቀነሱ ተጫዋቾች ለቀረበላቸው ጥያቄ…

”የሚቀነሰው ተጫዋች ዛሬ ማታ ነው የሚታወቀው። ምክንያቱም አሁን ልምምድ አለን። ( ቃለ ምልልሱ የተደረገው ቀን 9 ሰዓት ላይ ነው ) የሚገጥመን ነገር ስለማይታወቅ ማለት ነው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ነው አሁን ቀድመህ ይፋ ብታደርገው ከዛ በኋላ አንድ ነገር ቢያጋጥም አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ከልምምድ በኋላ እናሳውቃለን። ከዛ ውጪ ሁለት ነው የሚቀነሰው። ብዙም አስቸጋሪ ሊሆን የሚችል አይደለም።”

በተደጋጋሚ ስለሚነሳው የአጥቂ ችግር እና በዚህኛው ጨዋታ እሱን ለመቅረፍ ስላቀዱት ዕቅድ…

”የአጥቂ ችግር እንደምታውቁት ሁላችንም የምናውቀው ችግር ነው። ከዚህ ቀደምም ያወራነው ነገር ነው። ግን ያለንን አቅም ነው የምንጠቀመው። ስለዚህ አሁን ከዚህ ቀደምም የሞከርናቸው ብዙ ልምምዶች ተሰጥቶ የታዩ ተጫዋቾችን ይዘን ለመጓዝ አልፈለግንም። ምክንያቱም ታይተዋል ብዙ በሙከራ እና በጨዋታም ደረጃ ማለት ነው። ተጫውተው ዐይተናቸዋል ስለዚህ እዛ ላይ በነበረው ነገር ኤፌክቲቪ የሆነ ነገር ስላላሳዩን እነሱን ትተን አዲስ ተጫዋቾችን ይዘናል ለምሳሌ አቤል ያለውን አሁን በሙሉ ጤንነት አግኝተናል ፤ በሀሰተኛ 9 ቁጥር ሳይሆን በሙሉ አጥቂ ነው የምንጫወተው መሐመድኑር ናስርም ስላለ የፊት መስመሩን ያጠናክሩልናል።”

በዚህ በሦስት እና ሁለት ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የምፈልጋቸውን ነገሮች የሚያሟሉልኝን ተጫዋቾች ተመልክቻለሁ ብለው ያስባሉ…?

”ያው የምታውቁት ነው። ከዚህ በፊትም ደጋግመን እንደተነገረው። አንድ ተጫዋች በየጊዜው አቅሙ እየቀነሰም እየወረደም ይመጣል። በእነዚህ ሁለት እና ሦስት ጨዋታዎች የታዩ ተጫዋቾት ያው ከዚህ ቀደምም የምናውቃቸው ስለሆኑ ያንን ድምር ግምት ውስጥ አስገብተን ነው የመረጥናቸው እንጂ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ጨዋታዎች ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደምም በምናውቀው ማለት ነው። ያንን አሁን ደግሞ በሁለት እና በሦስት ጨዋታ ላይ የታዩ ጎላ ብለው ጥሩ ነገር ያሳዩ ተጫዋቾችን ጨምረናል። ከዚህ አንፃር የተወሰነ ነገር እናያለን ብለን እናስባለን። አሁን ልምምድ ላይ እንዳለፈው የነበረብኝ ችግር ምንድነው የፕሪ ሲዝን ወቅት ስለነበረ ሙሉ አቅማችንን በአንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርገን እንዳንሠራ አድርጎናል። ፊዚካል ፊትነሳቸው የተሟላ አልነበረም። አሁን ግን ብዙዎቹ የፊዚካል ፊትነስ ችግር የለባቸውም። አሁን ሞር የታክቲክ እና የሲስተም ጨዋታ ላይ ብቻ ትኩረት እያደረግን እየሠራን ነው ያለነው። አሁን በምናየው ነገር ጥሩ ነው። በተወሰነ ጊዜ የሜዳው ጥራት እና የሳሩ አለመታጨድ ትንሽ አስቸግሮን ነበር። ግን ከትናንትና ጀምሮ ታጭዷል። ትናንትና እና እንግዲህ ዛሬም እናየዋለን። የሚታዩ ነገሮች በጣም ጥሩ ናቸው። ኢቭን ኢፍ ሳሩ በጣም ከፍ ብሎም የሚያሳዩት ጉልበት የሚጠይቅ ነው አድካሚ ነው በጣም አስቸጋሪ ነበር። ነገር ግን የሚያሳዩት ጥረት የምንፈልገውን ጨዋታ ለመተግበር የሚያደርጉት ጥረት በጣም ጥሩ ነበር እና እንደማስበው ጥሩ ነገር ያሳያሉ ብዬ አስባለሁ።”

ከዚህ ቀደም ቡድኑን ማሰልጠን ሰልችቶኛል እያሉ ስለሰጡት አስተያየት እና እየሰለቻቸው ማሰልጠን ውጤት ላይ ስለሚያመጣው ተፅዕኖ ተጠይቀው…

”በነገራችን ላይ ሰለቸኝ ማለት ሁለት ቡድን ማሰልጠን ሰለቸኝ ነው። ሁለት ቡድን ማሰልጠን አስቸጋሪ ስለሚሆን ማለት ነው። በቀጣይም ከዚህ በኋላም ሁለት ቡድን ማሰልጠን አልችልም። ፍላጎቱም አይኖረኝም። ምክንያቱም አስቸጋሪ ስለሚሆን ማለት ነው።”

ችግር እንደሚኖረውስ አያውቁም ነበር…?

”አውቃለሁ። ነገር ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ችግር ነበረበት በነበረበት ወቅት ማለት ነው። ችግሩን መጋራት ስለነበረብኝ ነው እስከተወሰነ ጊዜ ለአንድ ዓመት ያህል ቢያንስ ችግሩን መጋራት እችላለሁ ብዬ ነው የገባሁት። ያው ያለውን ነገር ማለት ነው። ነገር ግን በሂደት ስታየው ሁልጊዜ አንድ ነገር ስትገባበት እና ከውጪ ሆነህ አንድ አይደለም። ዞሮ ዞሮ ግን በተቻለኝ መጠን ማኔጅ ለማድረግ ጥረት አድርጌያለሁ። ቢሆንም ግን በዚሁ መቀጠል አለበት ብዬ ስለማላምን ነው ለዛ ነው። ይሄ የመሰላቸቱ ሁኔታ ለመሥራት ሳይሆን ሁለቱንም ቡድን ማሰልጠን ከባድ ስለሚሆን ነው መሰላቸት የሚያመጣው ማለት ነው።”

ስህተት ነበር ማለት ነው…?

”እኔም ጋር ሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስህተት የለም። ካለው ችግር አንፃር መጋራት አስፈላጊ ስለሆነ ማለት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ መሥራት ስላለብኝ ነው እንጂ መጀመሪያውኑ በጣም ረጅም ጊዜ ወስደናል በዚህ ጉዳይ ላይ ማለት ነው። ነገር ግን አማራጮች ጠባብ ስለነበሩ በዛ ምክንያት እኔም ደግሞ ላግዝም እንደሚገባኝ ስለተነገረኝ በዛ ምክንያት ሁላችንም ገብተናል ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ነው።”