ከዋልያዎቹ ስብስብ ሁለት ተጫዋቾች ተቀንሰዋል

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ወደ አቢጃን ከሚያቀኑት የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ሁለት ተጫዋቾች መቀነሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ አቻው ጋር የምድቡን ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታ ለማድረግ ነገ ወደ አቢጃን የሚጓዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ከተደረገላቸው 25 ተጫዋቾች መካከል ሁለት ተጫዋቾች እንደሚቀነሱ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሳውቀው ነበር። ይሁን እንጂ አሰልጣኙ ሁለት ተጫዋች እንደሚቀነሱ ቢናገሩም ስለተቀነሱት ተጫዋቾች ስም ያሉት ነገር የለም።

ሶከር ኢትዮጵያ ማምሻውን ባደረገችው ማጣራት ባሳለፍነው እሁድ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ጥሪ የተደረገላቸው አማካዩ ጃዕፈር ሙደሲር እና አጥቂው ፋሲል አስማማው ከቡድኑ ጋር ነገ ወደ አቢጃን እንደማይጓዙ እና መቀነሳቸውን አረጋግጠናል።

በሌላ ዜና አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ቡድኑን በመቀላቀል ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን መሥራቱንም ሰምተናል።

ዋልያዎቹ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ነገ ማለዳ ወደ አቢጃን የሚያቀኑ ሲሆን ጥቀምት 2 ቀን ምሽቱ 1፡00 እና ጥቅምት 5 ቀን ምሽት 4:00 አቢጃን በሚገኘው ስታድ ደ ኢቢምፔ ሜዳ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።