ሪፖርት | ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን ረታለች

ቀይ ቀበሮዎቹ ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ሰለሞን ገመቹ፣ ዳግም አወቀ እና ናትናኤል ሰለሞንን አስወጥቶ በዮሐንስ መንግሥቱ፣ ቢኒያም በቀለ እና ኩሩቤል ዳኜ ተክቶ ጨዋታውን ሲጀምር ዋልያዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በሙከራም ሆነ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶባቸዋል። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱት ደቡብ ሱዳኖች ሁለት ለግብ የቀረበ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በ14ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ርዎቶምዮ ኦዶንግ በኳስ ቅብብል ስህተት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው ንጎንግ ጋራንግ በተከላካዮች መሃል ገፍቶ በማስቆጠር ሀገሩን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ካስተናገደ በኋላ ሙሉ ብልጫ መውሰድ የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኳስ ቁጥጥር ረገድ ብልጫ መውሰድ ቢችልም የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻለም፤ ኪሩቤል ዳኜ የግብ ጠባቂውን መውጣት ዐይቶ መቷት ከአግዳሚው በላይ ለጥቂት የወጣችው ሙከራ እና በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው አብዱሰላም የሱፍ  ከዮሐንስ መንግሥቱ የተቀበላትን ኳስ ቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው ያወጣት ኳስም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ደቡብ ሱዳኖች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ በርዎቶምዮ ኦዶንግ አማካኝነት ያደረጓት የግንባር ሙከራም የቡድኑን መሪነት ለማስፋት የተቃረበች ነበረች።

ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት  ሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የተስተናገዱበት ነበር። ደቡብ ሱዳኖች ከማዕዝን ምት ተሻግሮ በግብ ጠባቂው በተሠራ ጥፋት ምክንያት በተሻረ ግብ የአጋማሹ የመጀመርያ ሙከራቸው ሲያደርጉ በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በተለይም ግብ አስቆጣሪው ንጎንግ ጋራንግ ሞክሯት ዐብዩ በጥሩ ሁኔታ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ ለግብ የተቃረበች ነበረች።

ደቡብ ሱዳኖች ከተጠቀሱት ሙከራዎች በኋላም በ74ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ዳንኤል ቢቺኦክ ከማዕዝን ምት የተሻገረችውን ኳስ በግንባሩ በማስቆጠርም የቡድኑን መሪነት አደላድሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ቀይ ቀበሮዎችም በ82ኛው ደቂቃ በዋንጫ ቱት አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ተከላካዩ ተቀይሮ የገባው ያሬድ ብሩክ ከማዕዝን ምት የተቀበላትን ኳስ አሻግሮለት በመምታት ነበር ግቧን ያስቆጠረው። ቀይ ቀበሮዎች በመጨረሻ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ በሦስት አጋጣሚዎች አቻ የሚሆኑበት ዕድልም አግኝተው ነበር፤ በተለይም ናትናኤል ሰለሞን ግብ ጠባቂው ኳስ ለማስጣል በወጣበት አጋጣሚ ያገኛትን ኳስ መቶ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ኳስ ኢትዮጵያን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች።

ውጤቱን ተከትሎ ቀይ ቀበሮዎች ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው በቀጣይ ዓርብ ቡሩንዲን የሚገጥሙ ይሆናል።