ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ የተደረገባቸው ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን ለፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ልከዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ወልቂጤ ከተማ የቀረበውን የይግባኝ አቤቱታው የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜ ገደብ እና ግዴታዎችን ያላሟላ በመሆኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አቤቱታውን እንዳልተቀበለው ማሳወቁ ይታወቃል።
የይግባኝ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው ወልቂጤ ከተማዋች አራት ገፅ የያዘ ደብዳቤ በመያዝ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ “ትክክለኛ ፍትህ ይስጠን” በማለት አቤቱታቸውን አስገብተዋል። ወልቂጤዎች የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ጊዜውን ያልጠበቀ ነው በማለት የወሰነው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲሉ በዋናነት የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበዋል።
ወልቂጤዎች የውሳኔው ደብዳቤው መስከረም 21 ቀን ደርሷቸው ያሏቸውን 7 ይግባኝ የማስገቢያ ቀናት ዕድል ተጠቅመው መስከረም 23 ቀን ይግባኝ ማስገባታቸውን በመጠቆም ይግባኝ የማስገቢያ ጊዜው አልፏል በሚል ምላሽ ውድቅ ስለመደረጉ ፣ ክለቡ ወደ ውድድር ተመዝግቦ ሳይገባ የገንዘብ እና የነጥብ ቅነሳ መደረጉ ባልተመዘገበ ክለብ ይህ ድርጊት መፈፀሙ የህግ ጥሰት መሆኑን ፣ ክለቡ ለሚመለከታቸው ግለሰቦች ደመወዝ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ፣ ክለቡ በፌዴሬሽኑ የተሰጠውን ውሳኔ ለመፈፀም እና ለማጠናቀቅ ሂደት ላይ በነበረበት ጊዜ የሊግ ካምፓኒው የሰጠው ውሳኔ ከህግ አግባብ የሆነ እና ተገቢ ያልሆነ እንደሆነ በመጠቆም አቤቱታቸውን አሰምተዋል። አቤቱታቸውንን የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል።