ከትናንት በስቲያ ወደ አቢጃን ካቀናው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ አንድ ተጫዋች ጉዳት ማስተናገዱ ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የምድቡን ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታውን ከጊኒ አቻው ጋር ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ወደ አቢጃን 23 ተጫዋቾችን በመያዝ የተጓዘ ሲሆን ትናንት የሁለተኛ ቀን ልምምዱን በ ሊሴ ሞደርን ‘ኮኮዲ ት/ቤት ሜዳ አከናውኗል። ቡድኑ ትናንት ባደረገው ልምምድ ላይ አማካዩ ቢኒያም በላይ በጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ልምምድ ሳይሠራ መቅረቱን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ቢኒያም ከጉዳቱ በመነሳት ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 2 ቀን ከጊኒ ጋር ለሚያደርገው የምድቡ ሦስተኛ ጨዋታ እንደማይደርስ ተረጋግጧል። ምን አልባት በሕክምና ክፍሉ በኩል በምድቡ አራተኛ ጨዋታ ማክሰኞ ጥቅምት 5 ቀን ሊደርስ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሏል። ሆኖም ቢኒያም ካጋጠመው ጉዳት ለማገገም ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት ዕረፍት የሚፈልግ በመሆኑ ለሁለተኛው ጨዋታ የመድረስ ዕድሉም ጠባብ እንደሆነ ተገምቷል።