ከውድድሩ መሰናበቱን ቀድሞ ያወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ከቡሩንዲ አቻው ጋር ያከናውናል።
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራትን በአህጉራዊ የ20 ዓመት በታች ውድድር የሚወክሉ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመለየት እየተደረገ የሚገኘው የሴካፋ ውድድር ባሳለፍነው ዕሁድ በ9 የቀጠናው ሀገራት መካከል በታንዛኒያ መካሄድ ጀምሯል።
በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከተጫዋቾች ጥሪ ጀምሮ ሲነሱ ከነበሩ የእድሜ ተገቢነት ጥያቄዎች አንስቶ እስከ ጨዋታዎቹ ውጤት እና እንቅስቃሴ ድረስ የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሱበት የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ያለውን ቆይታ ያገባድዳል።
በሁለት የምድብ ጨዋታዎች ከዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ተገናኝቶ በተከታታይ የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሁኑ ሰዓት የምድቡ ውራ በመሆን ያለምንም ነጥብ በ4 የግብ ዕዳ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በውድድሩ ህግ መሰረትም 3ኛ ጨዋታውን ከማረጉ በፊት ከውድድሩ መሰናበቱን አረጋግጧል።
በውድድሩ ህግ መሰረት እኩል ነጥብ ያመጡ ቡድኖች መጀመሪያ የግብ ክፍያቸው ከመታየቱ በፊት እርስ በርስ ተገናኝተው ባገኙት ውጤት መሰረት ደረጃቸው የሚወሰን ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ ምናልባት የዛሬውን የብሩንዲ ጨዋታ እንኳን ቢያሸንፍ ከበላዩ ካሉት ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጋር በእርስ በርስ ግንኙነት በመረታቱ እንዲሁም 1ኛ እና 2ኛ የሆኑ ቡድኖች ብቻ የሚያልፉ በመሆኑ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፉ ዕድል ያበቃለት ሆኗል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመርሐ-ግብር ማሟያ የሆነውን የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ 10 ሰዓት በአዛም ኮምፕሌክስ ከቡሩንዲ አቻው ጋር የሚያከናውን ይሆናል።