የሊጉ አክሲዮን ማኅበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያደርጋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በሳምንቱ መጨረሻ የሚያደርግ ይሆናል።

ምስረታው አምስት ዓመት ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር 5ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 2 ቀን በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል እንደሚያደርግ ታውቋል።

በጉባዔው ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እና ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ሲጠበቅ የ2016 የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 እቅድ በአክሲዮን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ  አቶ ክፍሌ ሰይፈ በቅድመ ተከተል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት እንደሚፀድቅ እና በተጨማሪም የ2016 የሂሳብ ሪፖርት፣ የውጭ ኦዲት የማሰየም ተግባርም ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘቸው መረጃ ከሆነ አዲስ በወጣው የ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ደንብ የዕቅድ አፈፃፀሙን በተመለከተ በሚቀርበው ሪፖርት መነሻነት በትግበራው ዙርያ ክለቦች ጥያቄ እንደሚያነሱ ሰምተናል።

ከውድድር መሰረዙ ይፋ የሆነው ወልቂጤ ከተማ የአክሲዮን ማኅበሩ አባል በመሆኑ በመድረኩ እንደሚሳተፍ ታውቋል።