የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነገ እና ማክሰኞ የሚደረገውን የኢትዮጵያ እና ጊኒ ጨዋታ ለማስተላለፍ ዝግጅት ላይ የነበረ ቢሆንም የቴሌቪዥን መብቱን የሸጠው ተቋም ችግር እንደገጠመው ተሰምቷል።
የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ የአህጉራችን ሀገራት መደረግ የጀመሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ነገ እና ማክሰኞ ወሳኝ ጨዋታዎቹን ከጊኒ አቻው ጋር በተከታታይ ያከናውናል።
የሀገራችን ብሔራዊ ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የኢትዮጵያን ጨዋታ ጨምሮ የማጣሪያ ጉዞውን የማስተላለፍ መብቱን ከዋናው የምስል መብት ባለቤት ኒው ወርልድ በመግዛት የዋልያዎቹን አንደኛ እና ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ለአድማጭ ተመልካቾች ማድረሱ አይዘነጋም። ቀጣይ ጨዋታዎችንም ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ የነበረው ተቋሙ እስከ ትናንት አመሻሽ ጨዋታዎቹን ለተከታዮቹ እንደሚያደርስ እርግጠኛ የነበረ ሲሆን አመሻሽ ከኒው ወርልድ የደረሰው አስቸኳይ የኢሜል መልዕክት ግን ምናልባት ጨዋታዎቹ የሚተላለፉበት ዕድል እንደጠበበ ያሳያል።
ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረቦች በደረሰን መረጃ መሰረት ኒው ወርልድ “ከአቅሜ በላይ በተፈጠረ ችግር” ብሎ ባስቀመጠው የኢሜል መልዕክት መነሻነት ጨዋታዎቹ ሊተላለፉ እንደማይችሉ ተጠቁሟል። ምናልባት የምስል መብቱ ባለቤት አጋጠመኝ ያለው ችግር ከተፈታ ግን የሚተላለፍበት ዕድል እንደሚኖርም ተመላክቷል።