ነገ ምሽት 1 ሰዓት የሚደረገው የኢትዮጵያ እና ጊኒ ጨዋታ በባለሜዳው ሀገር አልቢትሮች ይመራል።
በአህጉራችን ትልቁ የብሔራዊ ቡድኖች የውድድር መድረክ ለመሳተፍ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ከጀመሩ ወራቶች የተቆጠሩ ሲሆን ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ደግሞ በቀጣዮቹ ቀናት የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ እየተሰናዱ ይገኛሉ።
በምድብ 8 ከጊኒ፣ ዲ አር ኮንጎ እና ታንዛኒያ ጋር ተደልድሎ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካት በወቅታዊ ደረጃ የምድቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሆነው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ቡድን የፊታችን ቅዳሜ እና ማክሰኞ ያለ ምንም ነጥብ ግርጌ ላይ ከሚገኘው ጊኒ ጋር ወሳኝ ጨዋታውን ያደርጋል።
በነገው ዕለት ምሽት 1 ሰዓት በአቢጃኑ ስታድ ደ ኢቢምፔ የሚደረገውን የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታም አይቮሪያዊ አልቢትሮች እንደሚመሩት ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ጨዋታውን በመሀል አልቢትርነት ክሌመንት ፍራንክሊን ፓን ሲመሩት ኮአብናን ፕሮስፈር አድዩማን እና ካሊሉ ባምባ በረዳትነት እንዲሁም ኩዋሲስ ፍሬድሪክ ቢሮ በአራተኛ ዳኝነት ተሳትፎ ያደርጋሉ።