ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት የዋልያዎቹ አለቃ ምን አሉ?

“ለማሸነፍ ነው ወደዚህ የመጣነው አቻም ሆነ ሌላ ውጤት ምንም አማራጭ የለውም”

“…አሁን ላይ ሁሉንም ነገር ለምደነዋል”

“እንደ ቡድን ቀጥተኛ እና ማጥቃት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ይዘን እንቀርባለን”

ነገ ምሽት 1 ሰዓት ከሚደረገው የጊኒ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በፊት የዋልያዎቹ አሠልጣኝ የቅድመ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው….

“ጨዋታው በጣም ፈታኝ ይሆናል። ጊኒን እንደምንገጥም እናውቃለን። በፊፋ ደረጃ ከእኛ ይበልጣሉ። አሁን ግን ጨዋታው በጣም ጠንካራ ይሆናል ፤ እኛም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ስለሆነ ማሸነፍ አለብን። ለማሸነፍ ነው ወደዚህ የመጣነው አቻም ሆነ ሌላ ውጤት ምንም አማራጭ የለውም።”

ከሜዳቸው ውጪ ስለመጫወታቸው…

“እንዳልከው በሀገራችን ምንም የመጫወቻ ሜዳ የለንም በአሁኑ ጊኒ ባለሜዳ ናት ቀጣዩ ጨዋታ ግን በሜዳችን መደረግ ነበረበት ግን አዲስ አበባ ላይ ሜዳ የለንም። ብዙ ጨዋታዎችን ከሀገራችን ውጪ አድርገናል። አሁን ላይ ሁሉንም ነገር ለምደነዋል። ነገ ጊኒን ስንገጥም ሦስት ነጥብ ለመውሰድ እንሞክራለን።”

ጊኒ በፊፋ ደረጃ ብትበልጣችሁም ተከታታይ ጨዋታ ተሸንፋለች። ከወቅታዊ ብቃቷ አንጻር…

“የሆነ ተፅዕኖ ይኖረዋል ግን ከእኛ የተሻሉ ናቸው አሁን ላይ ባለው የፊፋ ደረጃ እኛ 145ኛ ነን። ነገ ጠንካራ ጨዋታ ይሆናል ለጊኒም ቢሆን። ሦስት ነጥቡ ለሁለታችንም በጣም ያስፈልገናል ከዛ ውጪ አማራጭ የለንም። በሁለቱ ጨዋታዎች ከቻልን 6 ወይም 4 ነጥቦችን የግዴታ ማግኘት አለብን አልያ ዕድል አይኖረንም። ስለዚህ በጣም ጥሩ እና ክፍት ጨዋታ ይሆናል ምክንያቱም እነሱም ለማሸነፍ ነው የሚመጡት።”

በቴክኒካል ዕይታ ስለ ጊኒ ደካማ ጎኖች….

“ጊኒዎች ጠንካራ ጎን እንዳላቸው ሁሉ ደካማ ጎንም አላቸው። ያው ወቅታዊ ነገር ነው የሚወስነው ስለነገው ፎርሜሽናቸው የምናውቀው ነገር የለም። ስለዚህ በነገው ጨዋታ ጠንካራ የሆነው ያሸንፋል። ቴክኒካሊም ሆነ ታክቲካሊ ጥሩ ናቸው ግን ጨዋታውን ለማሸነፍ እንጥራለን። እንደ ቡድን ቀጥተኛ እና ማጥቃት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ይዘን እንቀርባለን። ከዚህ በፊት ከአጨራረስ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ነበሩብን ነገ ግን ጥሩ የአጨራረስ ብቃት እንደሚኖረን አስባለሁ። የተወሰነ የትኩረት ማጣት ችግርም ነበረብን። እዛ ላይ ስንሠራ ነው የከረምነው ነገ ለእኛ ጥሩ የሚሆን ይመስለኛል ፤ ሁሉንም ነገ ታያላችሁ።”

በጨዋታው ስለሚኖራቸው አቀራረብ…

“ቀድሜ እንዳልኩት ለማሸነፍ አጥቅተን ነው የምንጫወተው። የራሳችን ስትራቴጂ አለን ቢሆንም ለዛሬ ምስጢር ነው። እያንዳንዱን ነገር መናገር አስፈላጊ አይደለም። ነገ የሚፈጠረውን ታያላችሁ።”