ጉዳያቸው በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንዲታይ ጥያቄ ያቀረቡት ሠራተኞቹ ከእግርኳሱ የበላይ አካል ምላሽ ማግኘታቸው ታውቋል።
የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ ባለማሟላታቸው ተገቢ ተጫዋቾችን ይዘው ወደ ውድድር መቅረብ ያልቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች ከ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሰረዛቸውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድርና ስነስርዓት ካሳወቀና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እውቅና ከሰጠው በኋላ አቤቱታቸውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያቀረቡት ሲሆን አቤቱታቸውም በፌዴሬሽኑ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውድ መሆኑ አይዘነጋም።
የይግባኝ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው ወልቂጤ ከተማዋች አራት ገፅ የያዘ ደብዳቤ በመያዝ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ “ትክክለኛ ፍትህ ይስጠን” በማለት ባሳለፍነው ሳምንት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ለጥያቄያቸው ይፋዊ ምላሽ መስጠቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በዚህም ተቋሙ በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ የተቀመጠውን ደንብ በመጥቀስ የፍትህ አካል ውሳኔ የሰጡባቸውን ጉዳዮች የፌዴሬሽኑ ማንኛውም አካልም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የማየት ስልጣን የሌለው መሆኑን በማመላከት ምላሽ ሰጥቷል።