ወልዋሎዎች ከጋናዊው ጋር ተለያይተዋል

በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀናት ወልዋሎን የተቀላቀለው ጋናዊ ተከላካይ ከቢጫዎቹ ጋር ተለያይቷል።
የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ ቀናት አስቀድሞ ወልዋሎን የተቀላቀለው ጋናዊው ተከላካይ ሰሎሞን አዶማኮ ከቢጫዎቹ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል ፤ ተጫዋቹ የረዥም ጊዜ ጉዳት ያስተናገደውን እያሱ ለገሰ ለመተካት ቡድኑን ቢቀላቀልም በጉዳት ምክንያት ለቡድኑ ጨዋታ ሳያከናውን በጋራ ስምምነት ውሉን አፍርሷል።

ከቢጫዎቹ ጋር መለያየቱን ተከትሎ በትናንትናው ዕለት ወደ ሀገሩ ያቀናው ይህ ተከላካይ ከዚህ ቀደም በግሬት ኦሎምፒክ እና የእስራኤሉን ክለብ ሃፖኤል ኢሮኒ ሪሾን ሌዝዮን ማገልገሉ ይታወሳል።
ባለፈው የውድድር ዓመት በአልጀርያ በተዘጋጀው የቻን አፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻለው ይህ ተከላካይ በውድድሩ በመቐለ 70 እንደርታ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኘው ሸሪፍ መሐመድ ጋር በጣምራ ቡድኑን አገልግሏል።