የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አ/ማ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው የሊጉ አክሲዮን ማህበር አመራሮች ዛሬ ከቀትር በኃላ በተለያዮ ጉዳዮች ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር 6ተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል መካሄዱ ይታወሳል ፤ በዚህ መነሻነት የቦርድ ሰብሳቢው መቶ ዓለቃ ፍቃደ ማሞ እና የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በጋራ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ በዛሬው ዕለት በቤስት ዌስተርን ፕሪሚየር ዳይናስቲ ሆቴል ተሰጥቷል።

በጋዜጣዊ መግለጫው የተነሱ ዓበይት ጉዳዮችን አስቀድመን በተከታታይ በተለያዮ ርዕሶች ካጋራናቹሁ መረጃዎች በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮች የተነሱትን ሀሳቦች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።

የስፖንሰርሺፕ ጋር ተያይዙ ባሳለፍነው ዓመት ብዙ ርቀት ተሂዶ እና ተጠንቶ ከጫፍ የደረሰው ጉዳይ ለምን ሳይሳካ ቀረ ?

“እዚህ ላይ ብዙ ውስብስብ ነገሮች አሉበት በዚህ ድርድር ውስጥ የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አልነበረበትም ፤ ያልኖረበት ምክንያት እስከ እዚህ አመት አምስት ዓመት ማለት ነው የቴሌቭዥን ስርጭት እና የስም ሽያጭ ዲኤስ ቲቪ ውል አለው። በዚህ ጉዳይ ላይ በመሐል ገብቶ ነገሮችን ማተራመስ ስላልፈለግን እና መብታችንን ሊያሳጣን ይችል ስለነበረ በጉዳዩ ላይ እኛ አልገባንም። ይሁን እንጂ በሱፐር ስፖርት እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በመጨረሻም ስምምነቱ እክል ያጋጠመው ሱፐር ስፖርትን በሚወክል ኮንትራቱን ከዚህ ከኢትዮጵያ ማን ይፈርመው በሚለው ነው እንደምታውቁት መልቲቾይስ የሚባለው ሰፊ ድርሻ ባይኖረውም እዚህ ዲኮደር በመሸጥ በሚገኝ ገቢ የሚተዳደሩ እንዲሁም ከውጭ የሚመጣው ብር ዶላር ይመጣል ለእኛ በብር ይከፈላል በእነርሱ አልፎ ወደ እኛ ይመጣ ስለነበር በደስታ በጉዳዩ ላይ ተሳትፈው ነበር። ለምን ከጀርባው ለእነርሱ ብዙ ጥቅም ይገኝ ስለነበር ነው ፤ ይህን ጥቅም እናንተ ድረሱበት። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ እኔ ይሄን ያህል ሚሊየን ብር እከፍላለው እናተ ተረከቡ እና ለምትፈልጉት አካል  ክፈሉ ይሄ ደግሞ ብዙ ከንግድ ባንክ የሚረከቡት በብር ነው። በብር ተረክበው ለእኛ ሲከፍሉ ብዙ ግጭቶች ይፈጥራል። አንዱ የሀገር ውስጥ ገቢ ነው በብር ተረክበህ እንዴት ስለሚል እንዲህ ያለ ሪስክ ስላልፈለጉ አንፈርምም አሉ። የውጭው ደቡብ አፍሪካ ያለው አካል ደግሞ እዚህ መጥቶ እንዴት በብር ይከፈለኛል በማለቱ በዚህ ምክንያት  ነገሮቹ ሳይሳኩ ቀርተዋል።

የመጫወቻ ሜዳ ችግር ጉዳይ ?

“ይህ የሜዳ ችግር ጉዳይ ኮቪድ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን የሜዳዎች ሁኔታ እንመልከት የአዲስ አበባ ስታዲየም ኮቪድ ተብሎ ከተዘጋ በኋላ የካፍ እና የፊፋን መለኪያ እንዲያሟላ ተብሎ እድሳት ላይ ነው በሚል አራት ዓመት ተዘጋ ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ውድድር ደረጃውን ለማሻሻል በሚል ስታዲየሙ ተዘግቷል። ሁሉን ነገር አጠናቆ ከታህሳስ እስከ መጋቢት ብቁ ይሆናል ተብሏል። እንግዲህ ሲመጣ እናየዋለን። የመቐለ ስታዲየም በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበታል ፤ ሀዋሳ ብዙ ስታዲየሞች በዙርያው ቢኖሩም ደረጃውን የሚመጥን የለም። ትልቁ ስታዲየም ርክክብ አላደረግንም በሚል በጥቂት ምክንያቶች ቆሟል። ቢቸግረን ያለፉትን ዓመታት ዩኒቨርስቲ ሜዳዎች ጋር እየሄድን ልዩ ስምምነት እያደረግን እና ቴክኒካሊ እየተደጋገፍን ውድድሮችን አካሂደናል። አሁን ባለንበት ሁኔታ በዚህ ዓመት እጃችን ላይ ያለው ሜዳ አንደኛ ድሬደዋ እና ድሬደዋ ብቻ ነው። የአዳማ ስታዲየም ውሃ ማጠጣት፣ የመብራት ፣ የሰራተኛ ክፍያ ወጪ እጅግ ከፍተኛ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሜዳ አንድ ብቻ ነው። ሜዳው የካፍ እና የፊፋን መስፈርት ባያሟላም ለእኛ ይሆናል እንጠቀምበታለን። ግን ተገደን ነው በአንድ ሜዳ እንዲሆን የተደረገው ብለዋል።”

የዲኤስ ቲቪ ጋር ያላቹሁ የውል ዘመን በዚህ ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል በዚህ ዙርያ ለቀጣይ ምን ታስቧል ?

“ከትልቅ ተቋም ጋር ለአምስት ዓመት ከብዙ ተግዳሮቶች ጋር ውል አክብረን መጨረሳችን እጅግ የሚያስደስት ነው። በቀጣይ ከስያሜ መብት እና የቀጥታ ስርጭት የሚገዛን ተቋም ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት ረጅም ጊዜ ወስደን የምንሰራበት ነው።አሁን ካለው ጋር በአዲስ ኮንትራት ዙርያ ውይይት እናደርጋለን።እንዲሁም ካናል ፕሉስ ከዲኤስ ቲቪ ኮንትራቱን ለመግዛት ጥያቄ አቅርቧል። ይህ የተለያዩ ሂደቶች እያለፈ ነው። በቀጣይ በካናል ፕሉስ የበላይነት የሚጠናቀቅ ይመስለናል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መልቲቾይስ አፍሪካ ተጠሪነቱ ለደቡብ አፍሪካ መሆኑ ቀርቶ ወደ ፓሪስ ይሄዳል ማለት ነው። ብዙ ውስብስብ የሆኑ የግዢ እና የሽያጭ ሁኔታዎች እየሄዱ ነው። በዚህ ሂደት እኛ የት እንወድቃለን የሚለውን የራሳችንን ጥናት እያጠናን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ገንዘብ የምናገኝባቸው መንገዶች እየፈጠርን ነው በተለይ የማኀበራዊ ሚዲያ እንሰራለን በቀጣይ አመት የምንሰራው አንዱ ስራ ነው። በስታዲየም ጋር ባለው የትኬት ሽያጭ በተመለከተ የነበረውን  መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ መቻሉን እና የተሻለ ገቢ የሚገኝበትን በስታዲየም በር የትኬት አሻሻጥ ስርአት በመዘርጋቱ ተጠቃሚ መሆን ችለናል። ከእግርኳስ አስተዳደር ወጥተን አትራፊ ተቋም መገንባት እየቻልን ነው።”

በዚህ ዓመት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ስለሚያገኙ ጨዋታዎች በተመለከተ ??

“ሱፐር ስፖርት በዚህ ዓመት ውሌን ብቻ ነው የምፈፅመው ብሎናል ይህም ማለት ውሉ የቀጥታ ሽፋን የሚያገኙት ከ60 በላይ ጨዋታዎች ነው። ከዚህ ቀደም ሙሉ ያስተላለፈበት አለ አንድ ሁለት ሦስት የቀነሰበት አለ ፣ መቶ ቤት ያስተላለፈበት አለ በዚህ ዓመት የተሻለ ገቢ ስሌለኝ ውሌን ብቻ እፈፅማለው ብሎ 72 ጨዋታዎች ብቻ  የቀጥታ ስርጭት ያገኛሉ። ሌሎችን ግን ከእነርሱ ጋር ንግግር እያደረግን ነው። የማይተላለፉ ጨዋታዎችን እኛ ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንችላለን። ስለዚህ ከእነርሱ ፍቃድ እየጠበቅን ነው። ፍቃድ ሲሰጠን ከፌስቡክ ውጭ  በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ውድድሮችን እናስተለላልፋለን።”