በሞሮኮ ለሚደረገው የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ መርሀግብር የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ከሁለት ቀናት በኋላ ዛሬ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊኒ አቻቸው 3ለ0 ተረተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከቀናት በፊት ካደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ስታደርግ ያሬድ ባዬ ፣ ፍሬዘር ካሳ እና አብነት ደምሴ ወጥተው ራምኬል ጀምስ ፣ ሚሊዮን ሠለሞን እና ወገኔ ገዛኸኝ ሲተኳቸው ጊኒዎች በበኩላቸው መጠነኛ ጉዳት በገጠመው ኢብራሂም ኮንቴ ቦታ አንቶኒ ኮንቴን ተክተው ቀርበዋል።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በተመለከትንበት ጨዋታ ዋልያዎቹ ኳስን በመያዝ መጠነኛ ብልጫን ለመውሰድ ጥረት ባደረጉበት ወቅት በተለይ በጥልቅ አጨዋወት ከነዓን ገና በጊዜ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። 14ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከግራ ወደ ውስጥ ካሻማት እና ከነዓን ደካማ ሙከራን ከሰነዘረ በኋላ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች በይበልጥ በሽግግር ወደ ግብ ክልል በሚጣሉ ኳሶች ፋታ የለሽ ጥቃትን መሰንዘር የጀመሩት ጊኒዎች በሄዱበት ቅፅበት መሪ የሆኑበትን ጎል 16ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከመሐል በቅብብል ወደ ግራ የተለጠጠችን ኳስ አምበሉ ኢሳንጋ ሲላ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ሴሩ ጎራሲ በግንባር ገጭቶ ሰይድ ሀብታሙ መረብ ላይ አሳርፏታል።
ለተጋጣሚያቸው የመጫወቻ ቦታን እያሰፉ የመከላከል አጥራቸው እየደከመ የመጣው ዋልያዎቹ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል ፣ ማዲ ካማራ በቀኙ የሜዳ ክፍል ከተገኘ የቅጣት ምት መሬት ለመሬት ያሻገራትን ኳስ አብዱላሂ ቱሬ ጨርፋት ወደ ግብነት ስትለወጥ ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላ ደቂቃው 22ኛ ላይ እንደደረሰ ጋቶች ፓኖም ሴሩ ጎራሲ ላይ በሳጥን ውስጥ ጥፋት ሰርተሀል በሚል የተሰጠውን አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት የቦሪሲያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ሴሩ ጎራሲ ለራሱ ሁለተኛ ባለፈው ካስቆጠረው ሦስት ግብ ጋር በድምሩ አምስተኛ ግቡን አክሏል።
ሦስት ጎሎችን ካስቆጠሩ በኋላ በተወሰነ መልኩየጥንቃቄ አጨዋወትን ተጋጣሚያቸው በመምረጡ ፈጠን ባሉ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ጨዋታ ለመግባት የሞከሩት ኢትዮጵያዎች አከታትለው በቸርነት ጉግሳ እንዲሁም በቅብብል ስህተት አቤል ያለው ነፃ ቦታ ሆኖ ያገኘውን እጅግ ያለቀለት አጋጣሚን በተመሳሳይ ሁለቱም ተጫዋቾች አግኝተው የግብ ዘቡን ሙሳ ካማራ መረብን ግን መድፈር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ከዕረፍት መልስ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ሐይሌ የመከላከል መዋቅራቸውን ለማሻሻል ወገኔ ገዛኸኝን በያሬድ ባዬ በመተካት ጨዋታው በተቀዛቀዘ መልኩ ዝግ ብሎ ቀጥሏል። ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ በንፅፅር ወረድ ያሉ ፉክክሮችን እያሳየን በተጓዘው ጨዋታ አቤል ያለው ከቅጣት በደረሰችው እና በግንባር ገጭቶ ሙሳ ካማራ ከያዘበት በኋላ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ለመንቀሳቀስ የጣሩት ዋልያዎቹ 50ኛው ደቂቃ ከነዓን ከቀኝ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት የሰጠውን ኳስ ቸርነት አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ሙሳ ከጎልነት አግዶበታል።
ብዙም የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ያስናፈቀን ይህኛው አጋማሽ ጥንቃቄን መርጠው ከማጥቃቱ ይልቅ ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን መስጠን የመረጡት በቀደመው የሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ “ሲላ” ተቀፅላ ስያሜ የሚጠሩት ጊኒዎች ኢትዮጵያ በአንድ ሁለት አጨዋወት በፍጥነት ሳጥን ሲደርሱ በተደጋጋሚ በማገዱ ረገድ ተሳክቶላቸው መመልከት ችለናል። በመጨረሻዎቹ ሀያ ያህል ደቂቃዎች በይበልጥ ለግብ ለመጠጋት የታተሩት ዋልያዎቹ 85ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከርቀቶ ከቅጣት ምት አደገኛ ሙከራን አድርጎ ሙሳ ካማራ በጥሩ ቅልጥፍና ካወጣበት ብቸኛዋ ጥራት ያላት አጋጣሚ መልስ ጨዋታውን በመጨረሻም 3ለ0 የጊኒ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
በምድቡ ቀደም ብላ ታንዛኒያን የረታችው ዲ አ ር ኮንጎ በአስራ ሁለት ነጥቦች የምድቡ የበላይ ሆና ለአፍሪካ ዋንጫው ማለፏን ስታረጋግጥ ጊኒ በስድስት እና ታንዛኒያ በአራት ነጥቦች እንዲሁም ኢትዮጵያ ደግሞ በአንድ ነጥብ በተከታታይ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተቀምጠዋል።