በአህጉራዊ ውድድሮች ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይጀምራል፤ ሁለቱን የነገ መርሐግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ
በመጨረሻው መርሐ ግብር ሽንፈት ያስተናገዱ ክለቦችን የሚያገናኘው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለት ጨዋታዎች አከናውነው ሦስት ነጥቦችን በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነብሮቹ በመጨረሻው ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ ከደረሰባቸው የሁለት ለባዶ ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። እርግጥ ነው ሀድያ ሆሳዕናዎች መቐለ 70 እንደርታን በመርታት ዓመቱን ጀምረው በሊጉ የመጨረሻ መርሐግብር ላይ ሽንፈት አስተናግደዋል፤ ሆኖም ግን በጨዋታው ያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸው እንቅስቃሴ እና የፈጠሯቸው ዕድሎች ቡድኑ ተሻሽሎ ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ጠቋሚ ነበር። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ጠጣር እና ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው አቀራረብ የነበራቸው ነብሮቹ በመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ግቦች ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በነገው ጨዋታ የኋላ ክፍላቸውን ማስተካከል ቀዳሚ ሥራቸው ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። ተጋጣሚያቸው ጠንካራ የፊት መስመር እና ስል የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን እንደመሆኑም በኋላ ክፍላቸው የሚያደርጉት ማስተካከያ ወሳኝ ነው። ኃይቆቹ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ቢያስቆጥሩም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ጥራት ግን አሁንም ትልቅ ግምት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ነው።
ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ሰብስበው በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኃይቆቹ እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ከሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሀዋሳ ከተማዎች በሊጉ በጨዋታ በአማካይ 1.3 ግቦች ያስተናገደ ያልተረጋጋ የመከላከል አደረጃጀታቸው የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ነው። ቡድኑ ከተቆጠረበት የግብ መጠን በተጨማሪም በጨዋታዎቹ ያስተናገዳቸው የሙከራዎች ብዛት ለተጠቀሰው ድክመት ሌላ ማሳያ ነው። የቡድኑ የባለፉት ጨዋታዎች ኮከብ ተጫዋች ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ መሆኑም ለቡድኑ ደካማ ጎን ተጨማሪ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በነገው ጨዋታ የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ማስተካከያ ከማድረግ በዘለለ እንዳለው የጥራት እና የጥልቀት ልቀት ውጤታማ መሆን ያልቻለው የፊት መስመራቸውን በማሻሻል ምላሽ መስጠት ግድ ይላቸዋል።
ከአጨዋወት ምርጫ አንጻር የሀድያ ሆሳዕና ጠጣር አቀራረብ ለሀዋሳ ከተማ የስጋት ነጥብ ይሆናል።
ኃይቆቹ በመልሶ ማጥቃት ከመስመሮች ወደ ግብ የሚደርሱበት ሁኔታም በተመሳሳይ ለነብሮቹ የኋላ ክፍል ተጨማሪ የትኩረት ነጥብ መሆኑ አይቀሬ ነው።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል በቅጣት የቆየው አማካዩ አስጨናቂ ፀጋዬ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ ግን ቡድኑን ቢቀላቀልም በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በሀዋሳ ከተማ በኩልም ዮሴፍ ታረቀኝ ከጉዳት ሲመለስ ቢኒያም በላይ ከብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረበት ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ለቡድኑ አገልግሎቱን አይሰጥም።
ክለቦቹ የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር በሊጉ አስር ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሀዋሳ 3 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና 1 አሸንፏል። በቀሪ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 16፣ ሀዲያ ሆሳዕና 13 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ መቻል
የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን በድል የተወጡትን እና ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ የሚያልሙ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።
በሀድያ ሆሳዕና ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ነጥቦች በመሰብሰብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ተከታታይ ድል አስመዝግበው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በአሠልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው መቐለ 70 እንደርታ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የሚጥር ቡድን እንደሆነም በጨዋታዎች ታይቷል። ቡድኑ ሽንፈት ባስተናገደበት የመክፈቻው ጨዋታ ላይ ኳስን ተቆጥሮ የመጫወት አዝማሚያ ቢያሳይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን በአመዛኙ የመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን ሽግግር ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ተከትሏል። ሆኖም አጨዋወቱ በጥቂት ተጫዋቾች ብቻ የሚተገበር መሆኑ የመልሶ ማጥቃት ውጤታማነቱን ቀንሶታል።
ምናልባት ቡድኑ የተገደበውን የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ ከፍ በማድረግ እንዲሁም የቡድኑ ተጫዋቾች የውህደት ደረጃ ጨዋታ ከጨዋታ እየተሻሻለ ከመጣ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ የሚያደርግበት ዕድል እንዳለ ቢታመንም የመከላከል አደረጃጀቱ ግን አሁንም ማሻሻያዎች ይፈልጋል። ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ማስተናገዱ ሲታይ በቁጥር ረገድ የከፋ ባይሆንም በጨዋታዎቹ የነበረው ተጋላጭነት ግን የመከላከል አደረጃጀቱ ለውጦች እንደሚሻ ያሳያል። ቡድኑ በነገው ዕለት ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን መግጠሙም ለመከላከል አደረጃጀቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲገባ የሚያስገድደው ሌላ ምክንያት ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ከጦሩ ጋር የተሳካ ዓመት ያሳለፉት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ አምስት የሚጠጉ ተጫዋቾችን በጉዳት ማጣታቸውን ተከትሎ በርከት ያሉ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመጀመርያው የሊጉ ጨዋታቸው በሲዳማ ቡና ሽንፈት አስተናግደው በሦስተኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ ሦስት ነጥቦች የሰበሰቡት መቻሎች እንደ ተጋጣሚያቸው መቐለ ሁሉ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ያልማሉ። ከአስር ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በኋላ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት መቻሎች የጦና ንቦቹን በረቱበት የመጨረሻ ጨዋታ በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ ቀን አሳልፈዋል። በነገው ዕለትም በተመሳሳይ ከተጋጣሚያቸው ያለፉት ጨዋታዎች አቀራረብ አንፃር የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንደሚይዙ ሲጠበቅ የተቀዛቀዘው የቡድኑ የማጥቃት አቅም ደረጃውን ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ባለፈው ዓመት ብዙ የማጥቂያ አማራጭ ያለው እና ውጤታማ የመስመር አጨዋወት የገነቡት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በዚህ የውድድር ዓመት ግን የቀድሞ የፊት መስመር አስፈሪነታቸው ቀንሷል። በነገው ጨዋታም የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ ለማድረግ ውስን ለውጦች ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።
መቐለ 70 እንደርታዎች ዮናስ ግርማይ እና መናፍ ዐዎልን ለረዥም ጊዜያት በጉዳት ሲያጡ የአብሥራ ተስፋዬ እና ቦና ዓሊም ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው፤ ከዚህ በተጨማሪ የኪሩቤል ኃይሉ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በአንፃሩ መቻሎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
መቐለዎች ወደ ሊጉ በመጡበት የ2010 የውድድር ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች መቐለ 70 እንደርታ 3 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን መቻል አንዱን አሸንፏል፤ በግንኙነቱ መቐለ 8 ሲያስቆጥር ጦሩ 4 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።