ሪፖርት | ምዓም አናብስቶቹ እና መቻሎች ነጥብ ተጋርተዋል

የምሽቱ የመቐለ 70 እንደርታ እና መቻል ጨዋታ 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

መቐለ 70 እንደርታ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የመጀመሪያ ድላቸውን በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሲያስመዘግቡ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ቦና ዓሊን አስወጥተው በሔኖክ አንጃው እና ብሩክ ሙሉጌታ ሲተኩ መቻሎች በአንፃሩ ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ቡድናቸው ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አልዌንዚ ናፊያን ፣ ነስረዲን ኃይሉ እና አማኑኤል ዮሐንስ አርፈው ውብሸት ጭላሎ ፣ ፍሪምፓንግ ሜንሱ እና በኃይሉ ግርማ በምትኩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ እየተመራ ምሽቱን የተካሄደው የቡድኖች መርሐግብር የመጀመሪያዎቹ የጨዋታው አስር ያህል ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን ለማየት የቻልንበት ቢሆንም በሂደት ግን መቻሎች ብልጫውን የያዙበት ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ደርሰው ከግራ ቦታ የቅጣት ምት አግኝተው ሽመልስ በቀለ ወደ ግብ ሲመታ ሶፎኒያስ ሰይፈ በተቆጣጠራት ኳስ አጋጣሚን ፈጥረው ቀዳሚዎቹ ቢሆኑም 10ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ደርሶ አደገኛ ሙከራን የሰነዘሩት ግን መቐለዎች ነበሩ። በመልሶ ማጥቃት ያሬድ ብርሃኑ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘበት ነፃ ኳስ አግኝቶ የግብ ዘቡ ውብሸት ጭላሎ በጥሩ ቅልጥፍና የአንድ ለአንድ ግንኙነቱን አሸንፏል።

30ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ታመነ በጉዳት በነስረዲን ኃይሉ ተቀይሮ ከመውጣቱ በስተቀር ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች ሲፈጠሩ ያላስተዋልበት ጨዋታ ቀጥሎ መቻሎች ከመሐል ወደ መስመር በቅብብል በሚለጠጥ አጨዋወት ብልጫውን ወስደው መታየት ቢችሉም ኳስን ሲያገኙ  በመልሶ ማጥቃት ፈጥነው ከራሳቸው ሜዳ ይወጡ የነበሩት ምዓም አናብስቶቹ በ37ኛው ደቂቃ የመሪነት ጎልን ወደ ቋታቸው ከተዋል። ሠለሞን ሀብቴ ከማዕዘን አሻምቶ ያሬድ ከበደ በግንባር ያቀበለውን ኳስ ሌላኛው ያሬድ ብርሃኑ በግንባር ገጭቶ መረቡ ላይ አስቀምጧታል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በተወሰነ መልኩ የጨዋታ ብልጫን በድጋሚ ወደ መያዙ የመጡት መቻሎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀኝ ሰብሮ ገብቶ የመታት እና የውጪውን መረብ ነክታ ከወጣችዋ አጋጣሚ በኋላ ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ መቻሎች የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ነበር መመለስ የቻሉት በኃይሉ ግርማ እና አቤል ነጋሽ ወጥተው አማኑኤል ዮሐንስ እና ከአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ መልስ ሀገሩን አገልግሎ በተመለሰው አብዱ ሙታላቡ ለውጥ ተደርጎባቸዋል። ከአጋማሹ መጀመር አንስቶ ጨዋታውን በአግባቡ ወደ ራሳቸው አድርገው ብልጫውን የያዙት መቻሎች 51ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ወደ መቐለ ሳጥን ከተከላካይ ጀርባ የተጣለን ኳስ ተከላካዩ ዘረሰናይ ብርሀኑ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ኳሷ አቅጣጫ ቀይራ በራሱ መረብ ላይ በማረፍ ጨዋታው ወደ አቻነት ሊቀየር ችሏል።

ጥንቃቄ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥተው ራሳቸው ላይ ጫናዎች እንዲበረቱ በሚያደርግ እንቅስቃሴ ውስጥ የገደቡት ምዓም አናብስቱ በድግግሞሽ በተጋጣሚያቸው ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም በቀላሉ ግን ግብ እንዲቆጠርባቸው ፍቃደኞች አልነበሩም። የበረከት ደስታን የጥልቅ አጨዋወት አዘውትረው በአጋማሹ በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ብልጫን የወሰዱት መቻሎች ከፈጠሯቸው ሙከራዎች በጉልህ በ77ኛው ደቂቃ በረከት ወደ ውስጥ ከግራው መስመር በኩል ሰብሮ ይዞ ገብቶ ወደ ውስጥ የላካትን አጋጣሚ ሽመልስ እና ምንይሉ በሚያስቆጭ መልኩ ሁለቱም ሳይጠቀሟት ቀርተዋል። ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ መቻሎች በሽመልስ በቀለ ጎል አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ ሲባል በረከት ደስታ ደግሞ ቡድኑን አሸናፊ የምታደርግ ነፃ ኳስን አግኝቶ ካመከነ በኋላ ጨዋታው በመጨረሻም በ1ለ1 ውጤት ተቋጭቷል።