መረጃዎች | 14ኛ የጨዋታ ቀን

የ4ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎችን በቀጣዩ ዳሰሳችን እናስመለክታችኋለን።

ስሑል ሽረ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ከሊጉ መቋረጥ በፊት ጠንካራ አቋማቸውን ያሳዩ ሁለት ክለቦችን የሚያገናኘውን የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ 10 ሰዓት ሲል ይጀምራል።

ከሦስት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት ስሑል ሽረዎች ከሀዋሳ እና ፋሲል ከነማ ጋር ካስመዘገቧቸው የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ብርቱ ፉክክርን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ከአራት ዓመታት በኋላ ርቀው ወደ ቆዩበት ሊግ ተመልሰው መልካም የሚባል አጀማመርን እያደረጉ የሚገኙት ሽረዎች ከብሔራዊ ቡድን ዕረፍት መልስ ከቆሙበት እንደሚቀጥሉ ቢጠበቅም ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማ ከመሆኑ አኳያ ግን ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ለመገመት አያዳግትም። በዕርግጥ ቡድኑ በዓመቱ መጀመሪያ አዳማ ከተማን በመልሶ ማጥቃት እና በመስመር በኩል ስል በሆነ እንቅስቃሴ መርታት ችሎ የነበረ ቢሆንም በቀጣዮቹ የሀዋሳ እና ፋሲል ጨዋታዎች ግን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ እና የአፈፃፀም ብቃቱ በውስን መልኩ ተቀዛቅዟል። በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድ ይከተላል ተብሎ ሲጠበቅ  አዲስ ፈራሚዎቹም ለቡድኑ ጥሩ ግብዓት ይሆናሉ ተብሎም ይገመታል። ሆኖም ተከላካይ መስመሩ በፈጣን ሽግግሮች በቀላሉ ግብ የማስቆጠር ችግር ከሌለበት ድሬዳዋ ከተማ የሚገጥመውን ፈተና መቋቋም ይጠበቅበታል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ስር ሁለት የሊግ ጨዋታዎችን አከናውነው በመቶ ፐርሰንት የማሸነፍ ጉዞ ውስጥ ያሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ከቆሙበት ለመቀጠል ነገ በሜዳቸው እና በደጋፊዎቻቸው ፊት ሦስተኛ የዓመቱ መርሐግብራቸውን ይከውናሉ። የሊጉ መሪዎች ጋር በስድስት ነጥቦች ተቀምጠው የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ ከሚወስዱት ብልጫ በኋላ በፈጣን አጥቂዎቻቸው ዕገዛ ሦስተኛ የሊግ ድላቸውን ወደ ቋታቸው ለመክተት በሚያደርጉት ጉዞ በስሑል ሽረ መፈተናቸው አይቀሬ ይመስላል። ቡድኑ ባከናወናቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የፊት መስመር ጥምረት መያዙ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው ቢያስገድድም በነጻነት ገብረመድኅን ከሚመራው ጠጣር የኋላ ክፍል ቀላል የማይባል ፈተና ሊያስተናግድ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ ኬቨን አርጉዲ እና ዐወት በሪሁን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። አዲስ ፈራሚዎቹ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ዊሊያም ሰለሞንን ጨምሮ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስቡን ይዞ የሚቀርብም ይሆናል።

በ2011 ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ ከተሰረዘው እና የአቻ ውጤት ከተመዘገበበት የ2012 ጨዋታ ውጭ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው በሁለቱም ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፤ በግንኙነቱ ሁለቱም ክለቦች በእኩሌታ አንድ አንድ ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች የሚያገናኘውን ሰላሳ ስምንተኛ የሊግ ግንኙነት ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።

የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን የሊግ አሸናፊ በመሆናቸው በአህጉራዊ መድረክ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የቀረቡት እና ካደረጓቸው ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች መልስ ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ ዕርከን የተመለሱት ኢተዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በዚሁ በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ምክንያት ሳይጫወቱ ከቆዩ በኋላ ባደረጉት የሦስተኛ ሳምንት የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ግን አርባምንጭ ከተማን 3ለ1 በመርታት ዓምና ካቆሙበት እንደቀጠሉ ፍንጭ ማሳየት ችለዋል። ሻምፒዮን ሆኖ ካጠናቀቀበት ዓመት የነበሩ ተጫዋቾች አሁንም በስብስቡ የሚገኙለት ቡድኑ ከፍ ባለ ግለት አርባምንጭ ላይ የተጠቀመውን ፈጣን አጨዋወት በነገውም ዕለት ለመድገም ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን በመሐል ለመሐል እና በፈጣን የጥልቅ አጨዋወት ነገም ድልን ለማስመዝገብ እንደሚገቡ ቢጠበቅም በመከላከል አደራደር በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ የሚጠበቀውን የቅዱስ ጊዮርጊስን የኋላ ክፍል ማለፍ ግን ግድ እንደሚሆንበት መናገር ይቻላል።

በሦስት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብን ብቻ ያሳኩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነገም ሌላ ሦስት ነጥብን ፍለጋ ከከተማቸው ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ወሳኝ የጨዋታ መርሐግብርን ያደርጋሉ። በፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ቡድኑ እስከ አሁን በነበሩ ጨዋታዎች የፈጠራ ችግር በጉልህ የሚነፀባረቅበትን የአጥቂ መስመር አዳዲስ ባመጣቸው ተጫዋቾች እየታገዘ ይህንን ቀዳዳ ሊደፍን እንደሚችሉ መናገር ይቻላል። ወደ መስመር ባጋደለ መልኩ የማጥቂያ መነሻቸውን አድርገው ለመጫወት የሚጥሩት ፈረሰኞቹ ነገም ይህን አጨዋወት እንደሚጠቀሙ ቢገመትም ባለፉት ጨዋታዎች የነበሩባቸውን ጉልህ የቆመ ኳስ መከላከል ድክመት ቀርፈው መግባት ግድ ይላቸዋል።

ኢትዮጵያ ንገድ ባንኮች ከዓምናው በተላለፈ ቅጣት ዩጋንዳዊውን አጥቂ ሳይመን ፒተርን በቅጣት ፈቱዲን ጀማልን ደግሞ በጉዳት ያጣሉ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዳዲሶቹን ተጫዋቾች ጨምሮ ሁሉም ለጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል።

ተጋጣሚዎቹ በሊጉ በነበራቸው 37 ያህል ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የበላይነት ያለው ሲሆን 24 አሸንፎ ፣ በ10 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ንግድ ባንክ 3 ጨዋታ አሸንፏል። ፈረሰኞቹ 68 ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሀምራዊዎቹ 20 ጎሎች አስቆጥረዋል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው በ1998 ዓ/ም ነበር።