ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ አሁንም አልተሸናነፉም፤ ቡድኖቹ የተሰረዘውን የ2012 ጨዋታ ጨምሮ ተከታታይ አራተኛ የአቻ ውጤታቸውን አስመዝግበዋል።
ስሑል ሽረዎች ከመጨረሻው ቡድን አብዱለጢፍ መሐመድን በአሌክስ ኪታታ ቀይረው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ምንም ሳይለውጡ ጨዋታውን ጀምረዋል።
በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክር ካስመለከተን በኋላ የኋላ ኋላ የብርቱካናማዎቹ ብልጫ የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት ቢሆኑም በጥራታቸው ላቅ ያሉ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በተለይም በአመዛኙ ከቀኝ መስመር መነሻ ባደረጉ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች በተጠቀሰው መንገድ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በ21ኛው ደቂቃም መሐመርኑር ናስር ከቀኝ መስመር ይዟት ገብቶ መቷት ግብ ጠባቂው የተፋትን ኳስ በግቡ አፋፍ የነበረው ቻርለስ ሙሴጌ ወደ ግብነት ለውጦ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ድሬዎች ከግቧ በኋላም በጨዋታው ዋነኛ የማጥቂያ መንገዳቸው በነበረው የቀኝ መስመር ዕድሎች ፈጥረዋል። ከእነዚህም ጀሚል በጥሩ የአንድ እና ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ይዟት ገብቶ መቷት በሁለት አጋጣሚዎች ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ያዳኗት ኳስ የቡድኑን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።
በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች በድሬዎች የኳስ አመሰራረት ችግር ያገኟትን ዕድል ከሞከሩ በኋላ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ የቆዩት ስሑል ሽረዎችም በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃ አቻ የሚሆኑበትን ወርቃማ ዕድል አባክነዋል፤ አላዛር አድማሱ በጥሩ ቅብብል የመጣችውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሯት ከግቡ አፋፍ የነበረው አሌክስ ኪታታ ያመከናት ኳስም ቡድኑን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ መልክ የነበረው እና ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ በወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የስሑል ሽረ ብልጫ የታየበት ነበር፤ በውጤቱም ሽረዎች በ55ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አላዛር አድማሱ ከሳጥኑ ጠርዝ በጥሩ ሁኔታ ያሻገራትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ብርሀኑ አዳሙ አስቆጥሯት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ከነዛ ውስጥም መሐመድኑር ናስር ከግራ መስመር የተሻገረችለትን ኳስ መቶ ሞይስ ፖዎቲ የተቆጣጠራት ኳስ የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች።
ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎም ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በአራቱም ሳይሸናነፉ አቻ መለያየት ችለዋል።