ሪፖርት | ፈረሰኞቹ እጅግ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3ለ2 አሸንፎ ወደ ድል ተመልሷል።


ባንኮች በ3ኛ ሣምንት አርባምንጭን 3ለ1 ሲያሸንፉ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ሲቀርቡ ፈረሰኞቹ በአንጻሩ በመቐለ 70 እንደርታ 1ለ0 ከተረታው ስብስባቸው ተመስገን ዮሐንስ ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና ዳግማዊ አርዓያን አስወጥተው ባሕሩ ነጋሽ ፣ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ እና አማኑኤል ኤርቦን አስገብተዋል።

ምሽት 1 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ሲችሉ 15ኛው ደቂቃ ላይም ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ፉዓድ ፈረጃ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በግራው የግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በመብዛት በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወታቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ 22ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፍጹም ጥላሁን ከሳጥኑ የግራ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ተገኑ ተሾመ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 44ኛው ደቂቃ ላይ በባሲሩ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ሲመልሰው አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ግን ቶሎሳ ንጉሤ አዲስ ግዳይ ላይ በሠራው ጥፋት የፍጹም ቅጣት ምት አግኝተው ራሱ አዲስ ግደይ በግብ ጠባቂው ግራ እጅ በኩል መትቶት ግብ ጠባቂው በኳሱ አቅጣጫ ቢወድቅም ሊደርስበት ባለመቻሉ ኳሱ መረቡ ላይ አርፏል።


ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመጣጣኝ ፉክክር ሲቀጥል 54ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን ሀሚድ በግሩም ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ኪቲካ ጅማ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር ባንኮችን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር ይህ መሪነታቸው ግን የቆየው ለሦስት ያህል ደቂቃዎች ነበር ፍጹም ጥላሁን ወደ ሳጥን ባሻገረው ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ከካሌብ አማንክዋህ ቀድሞ በመውሰድ እና ግብ ጠባቂውን ፍሬው ጌታሁንን አታልሎ በማለፍ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን ወደ አቻነት መልሷል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅን አስወጥተው ፉዓድ አብደላን ቀይረው ሲያስገቡ ይህ ውሳኔያቸውም 82ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ፉዓድ በግራ መስመር እየገፋ ወስዶ በግሩም ሁኔታ የቀነሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮታል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በተፈጠሩ ጸቦች የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ኤፍሬም ታምራት እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ በረከት ወልዴ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል።