መረጃዎች| 15ኛ የጨዋታ ቀን

የአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በነገው ዕለትም ይቀጥላሉ፤ ሁለቱን መርሀ-ግብሮች አስመልክተን ያዘጋጀናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በነገው ዕለት በታሪካቸው ለሀያ አንደኛ ጊዜ የሚገናኙት የጦና ንቦች እና ቡናማዎቹ በግቦች የተንበሸበሸ የእርሰ በርስ ግንኙነት አላቸው፤ በነገው ዕለትም በየፊናቸው ድሉን አጥብቀው ይፈልጉታል።

ሁለት ሽንፈቶች ያስተናገዱትና በሦስት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦች ሰብስበው 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም እንዲሁም ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ቡናማዎቹን ለመርታት ወደ ሜዳ ይገባሉ። በሊጉ በጨዋታ በአማካይ ሦስት ግቦች በማስተናገደ እጅግ መጥፎ የመከላከል ቁጥሮች ያስመዘገቡት የጦና ንቦቹ የመከላከል አደረጃታቸውን ማስተካከል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል። በነገው ጨዋታም በሁለቱም የሊግ መርሀ-ግብሮች ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት እንዳላቸው ያሳዩትና ሀዋሳ ከተማ ላይ ሦስት ግቦች አስቆጥረው ድል የተቀዳጁትን ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደ መግጠማቸው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የታየው የመከላከል ችግሮቻቸው መቅረፍ ግድ ይላቸዋል።

ሁለት ጨዋታዎች አከናውነው አራት ነጥቦች የሰበሰቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሀይቆቹን ባሸነፉበት ማግስት ተከታታይ ድል በማስመዝገብ በአሸናፊነት ለመዝለቅ ጨዋታውን ይጠባበቃሉ።

በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታቸው ላይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ የተጋሩት ቡናማዎቹ በመጨረሻው መርሀ-ግብር ካገኙት የመጀመርያ ድል ባሻገር ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች የመጠቀም የአፈፃፀም ችግራቸውን በውስን መልኩ ቀርፈዋል።
በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው የባለፉት ጨዋታዎች የመከላከል ድክመት አንፃር የቀለለ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል ተብሎ ቢገመትም በሀዋሳው ጨዋታ የታየው የአፈፃፀም ልቀት ማስቀጠል ግን ቀዳሚው የቤት ስራቸው መሆን ይገባዋል። ሆኖም ለቀጣይ ለስጋት ሊዳርጋቸው የሚችል አጀማመር እያደረጉ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ያስተናገደውን የኋላ ክፍል ድክመታቸውን ለመሸፈን የአጨዋወት መንገዳቸው ሙሉ ለሙሉ ለውጠው የሚገቡበት ዕድልም ስላለ ቡናማዎቹ የማጥቅያ አማራጮቻቸው ማስፋት ይኖርባቸዋል።

በወላይታ ድቻ በኩል በቅጣትም ሆነ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ተጫዋች የለም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ግን ኪሩቤል ደሳለኝ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ታውቋል።

በ20 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 10 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። በቀሪዎቹ ፍልሚያዎች ሁለቱም ክለቦች እኩል አምስት ጊዜ ተሸናንፈዋል። በእነዚህ 20 ጨዋታዎች አጠቃላይ 33 ጎሎች ሲቆጠሩ ቡናማዎቹ 17፤ የጦና ንቦቹ ደግሞ 16 ግብ በስማቸው አስመዝግበዋል።

አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ-ግብር ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከመጀመርያው ጨዋታ ሽንፈት በማገገም ባህርዳር ከተማን አንድ ለባዶ አሸንፈው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል ወሳኙን መርሀ-ግብር ያከናውናሉ።

በመጨረሻው መርሀ-ግብር የተጫዋቾችም ሆነ የአቀራረብ ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን የከወኑት አዳማዎች በነገው ዕለትም በዋነኝነት ከመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን ሽግግሮች በሚገኙ ዕድሎች ግብ ለማስቆጠር እንደሚያልሙ ይገመታል። ባህርዳር ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ ውስን ብልጫ ቢወሰድበትም የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ አወንታዊ ነገር ያሳየው ቡድኑ ነገም ውጤታማ ካደረገውን አጨዋወት የወጣ አቀራረብ ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም። ሆኖም እንደ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ዕድሎች የመጠቀም ክፍተቱ ማሻሻል ሌላው ከፊቱ የሚጠብቀው የቤት ስራ ነው። ከዚ በተጨማሪ በመጀመርያው ጨዋታ ሦስት ግቦች አስተናግዶ በሁለተኛው መረቡን ሳያስደፍር የወጣውና የተሻሻለው የመከላካል አደረጃጀት ጥንካሬ ማስቀጠል የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ተጨማሪ የቤት ስራ ነው።

የውድድር ዓመቱን ፈረሰኞቹ ላይ በተቀዳጁት ድል አሀዱ ብለው የጀመሩት አፄዎቹ ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤት በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ዐፄዎቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን አግኝቶ ከቅብብሎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቀዳሚ ምርጫቸው እንደሆነ ባለፉት ጨዋታዎች ታይቷል። ሆኖም በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ የታየው ዕድሎች የመፍጠር ውስንነት የቡድኑ ማጥቃት እንቅስቃሴ ገድቦታል። በነገው መርሀ-ግብርም በመጨረሻው ጨዋታ የተሻሻለ የኋላ ክፍል ጥምረት የገነባው አዳማ ከተማን እንደ መግጠማቸው የቡድኑን የፈጠራ አቅም ጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ የሚኖራቸው የመሀል ክፍል ስኬት ውጤቱን የመወሰን አቅም ይኖረዋል።

ዐፄዎቹ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ኳስ ከመያዝ ባለፈ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ስያደርጉም ይታያል፤ በነገው ጨዋታም አጥቂው ጌታነህ ከበደን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ለማስቆጠር ለተቸገረው ቡድን እፎይታ ነው። ከዚ በተጨማሪ
ቡድኑ አልፎ አልፎ ለመልሶ ማጥቃቶች ተጋላጭ የሚሆንባቸውን አጋጣሚዎች መቀነስ ይኖርበታል።

አዳማዎች ዳንኤል ደምሱ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። በአፄዎቹ በኩልም ጌታነህ ከበደ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሟል ከአምበሉ በተጨማሪም ጉዳት ላይ የነበሩት ብሩክ አማኑኤል እና አንዋር ሙራድ7 ወደ ልምምድ ሲመለሱ አቤል እንዳለ እና ቃልኪዳን ዘላለም በህመም፤ ዮናታን ፍስሃ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። ከቡድኑ ጋር የተያያዘ ሌላ መረጃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በቀጣይ ሰኞ ወደ ልምምድ እንደሚመለስ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ባደረጓቸው አስራ አምስት የእርስ በርስ ግንኙነቶች ፋሲል ከነማዎች አምስቱን በመርታት የበላይነት ሲይዙ አዳማዎች በአንፃሩ አራት ጨዋታዎችን አሸንፈው የተቀሩት ሰባት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ።