ወልቂጤ ከተማ በምን ውድድር ይሳተፋል?

ሠራተኞቹ በየትኛው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ክፍል በኩል የወጡ አስገዳጅ መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው እና የፍቃድ ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ከፕሪምየር ሊጉ የተሰረዙት ወልቂጤ ከተማዎች አቤቱታቸውን ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቢያቀርቡም ውድቅ እንደተደረገባቸው ይታወሳል።

አሁን ላይ ክለቡ ለተጫዋቾች በስምምነት ቀሪ ደሞዛቸውን መክፈሉ የታወቀ ሲሆን እስካሁን ድረስ የቡድኑ አስራ አምስት ተጫዋቾችን በመያዝ በአሰልጣኝ ሶሬሳ ድጉማ እየተመሩ በድሬዳዋ ከተማ ዝግጅታቸውን ሲሠሩ የቆዩት ተጫዋቾቹ አዲስ አበባ ከቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ለመቀላቀል ዛሬ አልያም ነገ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለሱ ተሰምቷል።
የክለቡ ፕሬዝደንት ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳገለፁት ከሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ወልቂጤ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ እንዲሳተፍ ፍቃድ ለመስጠት ዛሬ ይዘውት የሚመጣው ሰነድ እንደሚጠበቅ የሰማን ሲሆን በቀጣይ ቀናት በየትኛው ምድብ ይካተታል የሚለው ይፋ የሚደረግ ይሆናል።