በዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ወላይታ ድቻ በያሬድ ዳርዛ የሁለተኛ አጋማሽ ሁለት ግቦች ከተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ ከኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል።
ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ወላይታ ድቻዎች በመቻል ሽንፈት ሲገጥማቸው ከተጠቀሙት ስብስብ ኬኔዲ ከበደ ፣ አብነት ደምሴ እና ፀጋዬ ብርሀኑን አሳርፈው አዛርያስ አቤል ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና መሳይ ሠለሞንን ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ሀዋሳ ከተማን 3ለ1 ከረታው ስብስብ ውስጥ ኤርሚያስ ሹምበዛን በስንታየሁ ዋለጬ በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሆኗል።
ዝግ ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ጎልን ያስመለከተን ገና 4ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ስንታየው ዋለጬ ከአማካይ ክፍሉ የደረሰውን ኳስ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ሆኖ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ኮንኮኒ ሀፊዝ በግንባር ገጭቶ በቢኒያም እና በተከላካዮች ተነካክታ የተመለሰችውን ኳስ አንነተህ ተፈራ ደርሳ በቀላሉ ኳሷን መረብ ላይ አሳርፎ ቡናማዎቹን መሪ አድርጓል።
ምንም እንኳን የጨዋታው ግለት ይቀዛቀዝ እንጂ ከራሳቸው ሜዳ በተዝናኖት በሚያደጓቸው አንድ ሁለት ቅብብል በቀላሉ ወደ ተቃራኒ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በተለይ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች የሚደርሱት ቡናማዎቹ 9ኛው ደቂቃ ኮንኮኒ ሀፊዝ ከቀኙ የሳጥን ጫፍ ሆኖ አክርሮ የመታት አደገኛ ኳስ ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ብቃት ከግብነት አድኗታል።
ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በተወሰነ መልኩ መቸገር ይስተዋልባቸው የነበሩት የጦና ንቦቹ በሂደት በረጃጅም ኳሶች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ አልያም በተጋጣሚያቸው በቅብብል ስህተት የሚፈጥሩላቸውን ኳሶች ተጠቅመው ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ማድረግን የጀመሩት ሲሆን በ13ኛ ደቂቃ ላይ በፍቃዱ አለማየሁ የተሳሳተውን ኳስ ካርሎስ ዳግምጠው ቢያገኝም ከግብ ዘቡ ኢብራሂም ዳላንድ ጋር ተገናኝቶ ጋናዊው የግብ ዘብ በንቃት ሲያስጥልበት በ15ኛው ደቂቃ ደግሞ ቡድኑ ከቀኝ ብዙአየው ወደ ቀኝ የሰጠውን ኳስ ፍፁም ግርማ ነፃ ቦታ ሆኖ ያገኛትን መልካም አጋጣሚ በኢብራሂም ዳላንድ በንቃት ተመልሶበታል።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን እያስመለከተን መጓዙን የቀጠለው ቀሪ የጨዋታው ደቂቃዎች ቡድኖቹ በመረጡት የጨዋታ አቀራረብ ወደ ግብ ክልል ለመድረስ የሚያደጉትን ጥረት ከማስተዋል በስተቀር ግልፅ የማግባት ዕድሎች ተፈጥረው ሳንመለከት አጋማሹ ተጋምሷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ድቻዎች የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ የጀመሩት ነበር ፤ አጋማሹን ከፍ ባለ ተነሳሽነት የጀመሩት የጦና ንቦቹ የአቻነት ግብን 48ኛ ደቂቃ ላይ ሲያገኙ ቴዎድሮስ ታፈሠ ከተከላካዮች በረጅሙ እግሩ ስር የገባችለትን ኳስ ወደ ግራ አዘንብሎ ለተገኘው ያሬድ ዳርዛ አቀብሏት አጥቂው ተፈጥሯዊ ባልሆነው ግራ እግሩ ጎሏን አስቆጥሯል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ ወረድ ያለ አቀራረብ የተከተሉት ቡናማዎቹ በይበልጥ በተከላካይ ክፍላቸው ላይ ያሳዩት ደካማ የመከላከል አቋቋም በመልሶ ማጥቃት የሽግግር አጨዋወትን መርጠው በታዩት ወላይታ ድቻዎች በድጋሚ ሊቀጡ ችለዋል።
66ኛው ደቂቃ መሳይ ሠለሞን ፍፁም ዝንጉ በነበሩት የቡና ተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ በድንቅ አጨራረስ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎ ቡድኑን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሸጋግሯል።
ከመጨረሻዋ ጎል በኋላ ከፉክክር ይልቅ መቀዛቀዞች በርክተው ማየት በቻልንበት ቀጣይ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች አቻ ለመሆን ድቻዎች በአንፃሩ በመረጡት የጥንቃቄ አጨዋወት ውጪ ተጨማሪ ነገር መመልከት ሳንችል ቀርተናል ይሁን እንጂ 84ኛው ደቂቃ ላይ የቡናማዎቹ አምበል እና ተከላካይ ራምኬል ጀምስ ከካርሎስ ዳምጠው ጋር ኳስን ለማስጣል ሲታገል ኳስን ለማግኘት ሲጥር በነበረው ቴዎድሮስ ታፈሠ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ በዕለቱ ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ከወጣ በኋላ በመጨረሻም ጨዋታው በወላይታ ድቻ የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።