ሪፖርት | በረከት ግዛው ዐፄዎቹን ታድጓል

በአስር ተጫዋቾች ረዘም ያሉ ደቂቃዎች ለመጫወት የተገደዱት አዳማ ከተማዎች በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ሙሉ ሦስት ነጥብ በመጨረሻም ተነጥቀዋል።

ከሁለተኛ ሳምንት በኋላ ወደ ወድድር የተመለሱተ አዳማ ከተማዎች ባህር ዳር ከተማን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ጋዲሳ ዋዶ እና ቻላቸው መንበሩ ወጥተው በምትካቸው አድናን ረሻድ እና መላኩ ኤልያስን ሲጠቀሙ በፋሲል ከነማ በኩል በተመሳሳይ ከሳምንታት በፊት ከስሁል ሽረ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ዮናታን ፍሰሃ እና አቤል እንዳለን አሳርፈው በምትካቸው በብሩክ አማኑኤል እና ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰውን አምበላቸው ጌታነህ ከበደን ተጠቅመዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዳማ ከተማ በመጀመሪያዎቹ 20 እንዲሁም ፋሲል ከነማ ደግሞ በቀሪዎቹ የአጋማሾቹ ደቂቃዎች የተሻለ ኳስ የተቆጣጠሩበት ነገርግን አደጋ መፍጠር ያልቻሉበት አጋማሽ ነበር ፤ በአጋማሹም የአዳማ ከተማው አማካይ አድናን ረሻድ በሁለት ቢጫ ከሜዳም የተሰናበተበት ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳን በቁጥር አንሰው የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በከፍተኛ ታታሪነት የጀመሩበት ነበር ፤ ነገርግን በሂደት የፋሲል ከነማዎች ማጥቃት አይሎ የተመለከትንበት አጋማሽ ነበር።

በ63ኛው ደቂቃ ግን እያየለ በመጣው የፋሲል ማጥቃት ውስጥ በአንድ ቅፅበት ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ቢኒያም አይተን በአስደናቂ የማፈትለክ ሩጫና በግሩም አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ፋሲል ከነማዎች አቻ ለመሆን በተለይም ከመስመሮች ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም የአዳማ ከተማው የግብ ዘብ ዳግም ተፈራ የሚቀመስ አልነበረም ፤ በተጨማሪም አዳማዎች አልፎ አልፎም ቢሆን በማጥቃቱ ረገድ እጅግ አስፈሪ የነበሩ ሲሆን በተለይም በ84ኛው ደቂቃ ቢኒያም አይተን እንደ መጀመሪያው ግብ ሁሉ አፈትልኮ በመሄድ ያደረጋት ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታበታለች።


ጨዋታው በአዳማ ከተማ ድል የሚጠናቀቅ በመሰለበት በ87ኛው ደቂቃ ዐፄዎቹ አቻ ሆነዋል ፤ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን የተላከውን ኳስ በሳጥን ጠርዝ የነበረው በረከት ግዛው ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ቡድኑን አቻ አድርጎ ጨዋታው ነጥብ በመጋራት እንዲቋጭ አስገድዷል።