“ኢትዮጵያ መልካም ዕድል እንዲገጥማት እመኛለሁ”
46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ገባኤ በዛሬው በመዲናችን አዲስ አበባ መከናወኑ ይታወቃል። ከመርሐ-ግብሩ መጠናቀቅ በኋላ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘደንት ፓትሪስ ሞትሴፔ (ዶ/ር) ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሀገር የብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ቆይታ እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ጉዳይ ዙሪያ ተጠይቀው አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያዊያን እግርኳስ ይወዳሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ ስለእግርኳስ ያላቸው እይታ ጥሩ እንደሆነ ገልፀው ኢትዮጵያ በይፋ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ባቀረበችው ጥያቄ መደነቃቸውን በማመላከት ኢትዮጵያ የካፍ መስራች እንደመሆኗ እንዲሁም እግርኳስ የሚወደድባት ሀገር እንደመሆኗ ውድድሩን ልታስተናግድ እንደምትችል ተናግረዋል። ይህ ቢሆንም ካፍ ባለው መመዘኛ መሰረት የኢትዮጵያ ዝግጅት ተገምግሞ ምላሽ እንደሚሰጥ በመጠቆም እንደ ሀገር ለቀረበው ጥያቄ መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ምኞታቸውን አጋርተዋል።