ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ከሦስት ነጥብ ጋር ተገናኝቷል

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአቤል ሀብታሙ ብቸኛ ጎል ባህር ዳር ከተማን 1ለ0 በመርታት የዓመቱን የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

በሊጉ የሦስተኛ ሳምንት መርሐግብር ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ጎል ጨዋታቸውን ፈፅመው በነበሩበት ወቅት ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ አሸብር ተስፋዬ ፣ እዮብ ገብረማርያም እና ፍቃዱ አለሙ ወጥተው ኢድሪሱ አብዱላሂ ፣ አባይነህ ፌኖ እና አቤል ሀብታሙ ሲተኩ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን ድል ካደረገው ቡድናቸው ባህር ዳሮች ግርማ ዲሳሳን በአምሳሉ ጥላሁን በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሆኗል።

10 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ መሪነት ለሦስተኛ ጊዜ ሁለቱን ቡድኖች በሊጉ ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በእንቅስቃሴ ወረድ ያሉ ፉክክሮች በይበልጥ በመጉላታቸው ወደ ሳጥን ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች አይናፋርነት ያጠቃቸው ሆኖ ተመልክተናል። በተወሰነ መልኩ ኳስን ለመቆጣጠር ከሚያልሙት የጣና ሞገዶቹ በተሻለ መልሶ ማጥቃት ላይ ስሎች እንደሆኑ ቀስ በቀስ ማሳየትን የጀመሩት ኤሌክትሪኮች 12ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያልታሰበች ጠጣር ሙከራን ከግራ በኩል አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ፔፕ ከመከተበት ከአራት ደቂቃዎች መልስ የመሪነት ግብ አግኝተዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ የቅጣት ምትን ባህር ዳሮች አግኝተው ፍፁም አሻምቶ በተከላካዮች ተገጭታ የተመለሰችን ኳስ በመልሶ ማጥቃት በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ አምርተው በመጨረሻም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እግሩ ስር የደረሰች ኳስ በጥሩ ዕይታ አቀብሎት የባህር ዳር የተከላካይ ክፍል የአቋቋም ስህተት አግዞት አቤል ሀብታሙ በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ቢሆኑም የማጥቂያ ሦስተኛው ክፍል ላይ ዕድሎችን መፍጠር ውስንነት ያለባቸው ባህር ዳሮች በ31ኛው ደቂቃ ቸርነት በይበልጥ ባደረገው የጥልቅ አጨዋወት ያቀበለውን ኳስ ሙጂብ ከአጠገቡ ለተገኘው ፍፁም ሰጥቶት ወደ ግብ በቀጥታ መቷት ኢድሪሱ አብዱላሂ አድኖበታል። በጨዋታው ላይ ብልጫውን ቢይዙም ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን በድግግሞሽ ያሳዩን ባህር ዳሮች 40ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የጨዋታ መንገድ ናትናኤል ያቀበለውን አቤል ሀብታሙ ነፃ ሆኖ አሁንም ያገኘውን አጋጣሚ ቢሞክራትም ፔፕ መልሶበት አጋማሹም በኤሌክትሪክ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

አማካዩ ፍቅረሚካኤል አለሙን በጄሮም ፊሊፕ በመተካት የአጥቂ ቁጥራቸውን በሁለተኛው አጋማሽ ከፍ አድርገው የተመለሱት ባህር ዳር ከተማዎች ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ በመቆጣጠር በቀላሉ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ሲደርሱ የታዩት 47ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። አምሳሉ ከቅጣት ምት አሻግሮ ፍሬዘር ካሳ አግኝቷት ኢድሪሱ አብዱላሂ ባወጣት ኳስ ሙከራን መሰንዘር የጀመሩ ሲሆን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በተመሳሳይ በርካታ ዕድሎችን ፈጥረው ግን የኢድሪሱ አብዱላሂን መረብ መድፈር ሳይችሉ ቀርተዋል።

መሳይ አገኘሁ እና ሙጂብ ቃሲም በጥሩ ቅብብል በተመሳሳይ ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ቢያደርጉም ንቁ በነበረው የግብ ዘቡ ኢድሪሱ መምከን ችለዋል። ማጥቃታቸውን ለዘብ አድርገው መከላከል ላይ በይበልጥ አመዝነው የተንቀሳቀሱት ኤሌክትሪኮች በውሀ ሰማያዊ ለባሾቹ ቢበለጡም ግባቸውን በንቃት መጠበቁ ላይ የዋዞች አልነበሩም። ፍፁም አለሙ 71ኛው ደቂቃ ላይ ካደረጋት አደገኛ ሙከራ በኋላም ደጋግመው ባህር ዳሮች ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች በተለይ በቀሪዎቹ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ውስጥ ቢያደርጉም አንዳች ነገር ተፈጥረው ሳንመለከትበት በኢትዮ ኤሌክትሪክ የ1ለ0 ውጤት ጨዋታው በመጨረሻም ተቋጭቷል።