ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብር በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡናዎች ድል ካደረገው ቋሚ አሰላለፍ መክብብ ደገፉ፣ ብርሃኑ በቀለ፣ ፍራኦል መንግስቱ፣ ያሬድ ባየህ፣ ሬድዋን ናስር፣ በዛብህ መለዮ እና ሳሙኤል ሳሊሶን አሳርፈው በቶማስ ኢካራ፣ ጊት ጋትኩት፣ ደስታ ዮሐንስ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን፣ ኢማኑኤል ላርዬ እና መስፍን ታፈሰ ተክተው ሲገቡ መድኖች በበኩላቸው ከኤሌክትሪክ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ ቡድን ያሬድ መሐመድን በአዲሱ ፈራሚ ረመዳን የሱፍ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት
የመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢያስመለክተንም በሙከራዎች ረገድ ግን የኢትዮጵያ መድኖች ብልጫ የታየበት ነበር። ዳዊት ተፈራ ከቅርብ ርቀት ከቅጣት ምት ባደረጋት ሙከራ የመጀመርያ የግብ ሙከራቸውን ማድረግ የቻሉት መድኖች በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው መሪ ሆነው የሚወጡበት ዕድልም አግኝተው ነበር። ዳዊት ተፈራ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች በኳስ ምስረታ ወቅት በሰሩት የቅብብል ስህተት ያገኛትን ኳስ ለወገኔ ገዛኸኝ አቀብሎት አማካዩ ኳስና መረብ አገናኘ ተብሎ ሲጠባቅ ወደ ጎልነት ያልቀየራት ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። ቡድኑ ከተጠቀሰች ሙከራ በኋላም በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሏል። አጥቂው በጨዋታው ሁለት የግብ ዕድሎችን የፈጠረው ዳዊት ተፈራ ከርቀት ያሻገረለትን ኳስ በሲዳማ ተጫዋቾች የተግባቦት ችግር አግኝቶ መቷት አግዳሚውን ለትማ የተመለሰችው ኳስም ሌላ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። በአጋማሹ በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም በቂ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት ሲዳማ ቡናዎችም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሀብታሙ ታደሰ ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአጋማሹም የመድኑ አማካይ ሀይደር ሸረፋ በገጠመው ከባድ ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ በመውጣት ተጨማሪ ሕክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል አምርቷል።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ መልክ የነበረው እና ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ መድኖች ብልጫ የታየበት ነበር። ሆኖም ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ነበሩ። በ52ኛው ደቂቃም ሀብታሙ ታደሰ ከማዕዝን ምት የተሻገረችለትን ኳስ በግንባር በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ በኋላ ሲዳማዎች አፈግፍገው ለመከላከል ሲሞክሩ መድኖች ሙሉ ብልጫ ወስደው በርከት ያሉ ሙከራዎችም ማድረግ ችለዋል።
ወገኔ ገዛኸኝ ዳዊት ተፈራ በጥሩ ሁኔታ አቀብሎት ወደ ግብነት ያልቀየረው ኳስ፤ መስፍን ዋሼ አሻምቶት አቡበከር ሳኒ ያልተጠቀመበት ዕድል እንዲሁም በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው ዳዊት ተፈራ ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ ያወጣው ኳስም መድኖች ከሞከሯቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። መሪ የሆኑበትን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በአመዛኙ ወደ ሳጥናቸው ቀርበው ለመከላከል የመረጡት ሲዳማ ቡናዎችም በመስፍን ታፈሰ እና ሳሙኤል ሳሊሶ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት ምት ሞክሯት አግዳሚውን ታካ የወጣች ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች።
ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብር በሲዳማ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ሊጉን መምራት ጀምሯል።