አዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ታውቋል

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ዋልያዎቹን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተመርጠዋል።

ላለፉት 12 ወራት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በጊዜያዊነት ብሄራዊ ቡድኑን ለመምራት ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በማሕበራዊ ትስስር ገፁ ይፋ እንዳደረገው አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድኑን በቻን ማጣርያ ጨዋታዎች እንዲመሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ወስኗል።
በተጫዋችነት ዘመኑ በክለብ ደረጃ ለአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ፣ ወንጂ ስኳር፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አየር ኃይል፣ ጥቁር ዐባይ በመጨረሻም በአርባምንጭ ውስጥ ተጫዋች እና ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እግርኳስን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ መጫወት የቻለው መሳይ  በአሰልጣኝነት ዘመኑ ወላይታ ድቻን ከምስረታው አንስቶ ከታችኛው ዲቪዚዮን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ትልቅ አስተዋፆ ያደረገ ሲሆን ከዚያ በኋላም በፋሲል ከነማ እና ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ያስቻለውን አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ከሰራ በኋላ በጊዜያዊነት ዋልያዎቹን ለማሰልጠን ተስማምቷል።
በተያያዘ ዜና በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ  ማጣርያ ኢትዮጵያ ከ ኤርትራ ጋር የምታደርጋቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በደቡብ ሱዳን ጁባ ብሔራዊ ስታዲየም የሚከናወኑ ሲሆን የጨዋታ ቀኖቹ ላይም ለውጥ ተደርጓል። በዚህም መሰረት ጥቅምት 21/2017 እና ጥቅምት 24/2017 ጨዋታዎቹ የሚከናወኑ ይሆናል።