ከፍተኛ ሊግ | ንብ የአስራ አራት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በአሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ የሚመሩት ንቦች የአስራ አራት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቁ የአምስት ነባሮችን ውል ደግሞ አድሰዋል።

ለ2017 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ “ለ” ስር ተደልድሎ የሚገኘው ንብ ለውድድር ዘመኑ ራሱን ለማጠናከር በአሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ እየተመራ በዝውውር መስኮቱ ላይ በመሳተፍ ወደ አስራ አራት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን ወደ አምስት ነባር ተጫዋቾቹን ውል ደግሞ አራዝሟል። በሱሉልታ ከተማ 3ለ1 በመረታት ከኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ውጪ መሆን የቻለው ቡድኑ በርካታ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ለቀጣዩ የሁለተኛው የሊግ ዕርከን ውድድሩ አስፈርሟል።

የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ ፣ መቻል ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሻሸመኔ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቆይታ የነበረው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ፣ የቀድሞው የዓየር ኃይል ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር ግብ ጠባቂ ሆኖ ያገለገለው ዮሐንስ በዛብህ ፤ በሀዋሳ ፣ ደደቢት ፣ ወልዋሎ ፣ ሲዳማ ቡና እና ያለፈውን ዓመት በሀምበርቾ የተጫወተው አማካዩ ብርሃኑ አሻሞ ፤ የቀድሞው የሀዋሳ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ አማካይ ሔኖክ ድልቢ ፤ በሲዳማ ቡና ፣ መቻል እንዲሁም ደግሞ በሀዋሳ የተጫወተው አማካዩ አዲሱ አቱላ ፤ በመቻል ላለፉት ሁለት ዓመታት የተጫወተው በኃይሉ ኃይለማርያም ወደ ቀደመ ክለቡ ዳግም ሲመለስ ፤ በአዳማ ፣ ሀድያ ሆሳዕና ፣ ድሬዳዋ እና አርባምንጭ በመስመር አጥቂነት ያገለገለው ሱራፌል ዳንኤል ፤ በሀድያ ሆሳዕና ፣ ሀዋሳ እና ኢትዮጵያ መድን መጫወት የቻለው ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሙ ፤ በነቀምት ፣ ሲዳማ ቡና ፣ መቻል እና ሰበታ የተጫወተው አጥቂው ገዛኸኝ ባልጉዳን ጨምሮ መኳንንት አሸናፊ አጥቂ ከሲዳማ ቡና ፣ ጌታለም ማሙዬ አማካይ ከሻሸመኔ ከተማ ፣ በድሩ ኑርሁሴን አጥቂ ከወልድያ ከተማ ፣ ሸሀብ መሐመድ ከአሶሳ ከተማ እና ሀሰን ዘለቀ ከወላይታ ድቻ ለቡድኑ የፈረሙ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ክለቡ የተከላካዩ አሌክስ ተሰማ ፣ የአማካዩ ኪዳኔ  አሰፋ ፣ የተከላካዩ ትኩሱ ጌታቸው ፣ የግብ ጠባቂው ግሩም በለጠ እና የአጥቂው ቡአይ ጆንን ውል ደግሞ ለተጨማሪ ዓመት አድሶላቸዋል።