አቡበከር ናስር ሌላኛውን የደቡብ አፍሪካ ክለብ በይፋ ተቀላቀለ

ኢትዮጵያዊው አጥቂ አዲሱ የሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ተጫዋች ሆኗል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ከደመቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን የቻለው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ አቡበከር ናስር በ2009 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጋር መተዋወቅ የቻለ ሲሆን በክለቡ በቆየባቸው ዘለግ ያሉ ዓመታትም ስኬታማ የሆኑ ጊዜያትን አሳልፏል። የ2013 የሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ ዕርከን ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ከሆነ በኋላ የሀገር ውጪ የእግር ኳሰ ህይወትን ለመምራት ወደ ደቡብ አፍሪካ በማምራት ለማሜሎዲ ሰንዳውስ ፈርሞ ቆይታን ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም እያስተናገደ ከሚገኘው ተደጋጋሚ ጉዳቶች የተነሳ ከክለቡ ጋር ከቀናት በፊት መለያየቱ ይታወሳል።

በቆይታው ዙሪያ ከሳምንታት በፊት ንግግር አድርጎ እንደነበር የሚታወሰው ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሌላኛውን የደቡብ አፍሪካ ክለብ የሆነውን እና በአሁኑ ሰዓት በደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪምየር ሺፕ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን ሱፐር ስፖርት ዩናይትድን በአንድ ዓመት ውል በይፋ ተቀላቅሏል።