ሪፖርት | ንግድ ባንኮች በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

የምሽቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሐግብር ወቅት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት የገጠማቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአራት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን ሲያደርጉ ተመስገን ተስፋዬ ፣ ኤፍሬም ታምራት ፣ ሱለይማን ሀሚድ እና ፉአድ ፈረጃን ከጉዳት በተመለሠው ፈቱዲን ጀማል ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ ብሩክ እንዳለ እና ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት በተመለሠው ሳይመን ፒተር ሲተኳቸው በአንፃሩ ከአዳማ ከተማ ጋር በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ነጥብ ተጋርተው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው በቡድናቸው ላይ ምንም ለውጥን ሳያደርጉ ለጨዋታው ቀርበዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ እየተመራ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱ መስመሮች የማጥቃት ምርጫቸውን በማድረግ የተንቀሳቀሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በይበልጥ በድግግሞሽ ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በጥልቅ የጨዋታ መንገድ ብልጫን ይዘው ሲያጠቁ ቢስተዋልም የአጥቂዎቻቸው የውሳኔ ስልነት ግን የተቀዛቀዘ ነበር። 6ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ዑመር ፈጠን ካለ የጨዋታ ምስረታ የደረሰውን ኳስ በተንጠልጣይ መልኩ ሲጥልለት ሳይመን ፒተር በአንድ ለአንድ ግንኙነት ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም በግብ ዘቡ ከማስ ኦባሶጊን ቅልጥፍና ከሽፎበታል።

ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት ዘለግ ላለ ጊዜ ተቸግረው የቆዩት አፄዎቹ በረጃጅም ኳስ በግራ እና ቀኝ የማርቲን እና ቢኒያምን እንቅስቃሴዎች በመጠቀም ጎል አስቆጥረዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ላንቃም በተደጋጋሚ ለማስከፈት ሲያደርግ የነበረው ጥረቱ ተሳክቶለት ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ወደ ግብ ኳሷን ሲመታ በቋሚ ብረቱ ተለትማ ስትመለስ ዩጋንዳዊው አጥቂ ማርቲን ኪዛ በቀላሉ እግሩ ስር የገባችለትን ኳስ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከወገብ በላይ የማጥቃት ደመ ነፍሳቸው ወጥ ይሁን እንጂ የፋሲልን የኋላ አጥር በቀላሉ መድፈር የተሳናቸው ንግድ ባንኮች ወደ ግብ ተስበው ቶሎ ቶሎ ሲደርሱ ብናይም የግቡን መረብ ማግኘቱ ላይ ግን አይናፋሮች ሆነዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ በአፄዎቹ በኩል ማርቲን ኪዛ ከግራ ወደ ውስጥ አሻምቶ ቢኒያም በግንባር ገጭቶ ከወጣችዋ አጋጣሚ በኋላ ብዙም ሙከራዎች ያልነበሩት አጋማሽም ተጠናቋል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳይመን ፒተርን በሱለይማን ሀሚድ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው እዮብ ማቲያስን በተካልኝ ደጀኔ በመተካት ነበር የተመለሱት። አጋማሹን ፈጣን በሆነው የኪቲካ ጅማ አደገኛ ሙከራ በማድረግ የጀመሩት ንግድ ባንኮች ከፍ ባለ ተነሳሽነት በሦስቱ ፈጣን አጥቂዎች ዕገዛ ከመሐል ለመሐል አልያም በመስመሮች በኩል በሚደረጉ የሰሉ ጥቃቶችን ቢሰነዝሩም አማስ ኦባሶጊን አልፈው መረቡን በማግኘቱ ረገድ ዕድለኞች አልነበሩም። ለተጋጣሚያቸው የኳስ ነፃነቱን ሰጥተው ጥንቃቄን መርጠው በመጠነኛ መልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚዳዱት አፄዎቹ 57ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ ነበር።

አዲስ ከቀኝ ወደ ውስጥ የሰጠውን ኪቲካ ከጀርባው ለመጣው ሱለይማን ቢሰጠውም የተጫዋቹ ጠንካራ ሙከራ በአማስ ኦባስጊ ልትከሽፍ ችላለች። ጌታነህ ከበደ በ72ኛው ደቂቃ በጥሩ የእግር ስራ ሳጥን ውስጥ ያገኛትን መልካም አጋጣሚ ወደ ግብ መቷት ፍሬው ካዳነበት በኋላ የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ጫናቸውን ከፍ ያደረጉት ሀምራዊ ለባሾቹ ቢሆኑም እንደነበራቸው ብልጫ ጎልን ማግኘት ላይ ግን ዕድለኞች መሆን ሳይችሉ ቆይተው በመጨረሻም የአቻነት ጎልን አግኝተዋል።

ኪቲካ ጀማ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ከተባለችው አጋጣሚም በኋላ በርከት ያሉ ሙከራዎችን የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ቡድኑ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የፋሲል የግብ ክልል የተገኘን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ፉዓድ ፈረጃ ሲያሻማ ኪቲካ በግንባር ጨርፎ ያደረሰውን ተስፋዬ ታምራት ቡድኑን 1ለ1 በማድረግ ጨዋታውም ተቋጭቷል።