መረጃዎች | 18ኛ የጨዋታ ቀን

የአምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ መቻል

ቢጫዎቹ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ጦሩ ደግሞ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

ሦስት ጨዋታዎች አከናውነው ምንም ነጥብ ያልሰበሰቡት ወልዋሎዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም መቻልን ይገጥማሉ። በሦስቱ ጨዋታዎች አንድ ግብ አስቆጥረው አራት ግቦችን ያስተናገዱት ቢጫዎቹ ባለፉት ጨዋታዎች ለስህተቶች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸውን ማስተካከል ቀዳሚ ሥራቸው መሆን ይገባዋል። ባለፉት መርሐግብሮች ተለዋዋጭ የተጫዋቾች ምርጫ የነበራቸው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሊጉ በተቋረጠበት ጊዜ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ  አግኝተዋል ተብሎ ስለሚጠበቅ የቡድናቸውን የውህደት ደረጃ ከፍ አድርገው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል። ይህንን ተከትሎም በአጨዋወትም ሆነ በተጫዋቾች ምርጫ ውስን ለውጦች ይጠበቃል።

በመጀመርያው ጨዋታ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ወላይታ ድቻን አሸንፈው ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር አቻ የተለያዩት መቻሎች ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ቢጫዎቹን ይገጥማሉ። ጦሩ የመጨረሻውን ጨምሮ ባለፉት መርሐግብሮች የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ቢችልም የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ጉልህ ድክመቶች ተስተውለውበታል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በነገው ዕለት ባለፈው የውድድር ዓመት የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ የነበረው የተለመደው አይምሬው የፊት መስመር ጥምረት ጥንካሬ መመለስ ዋነኛ ሥራቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በመጨረሻው ጨዋታ ለመልሶ ማጥቃቶች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ውስን ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት በተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር የበዛ እና በርከት ያሉ የግብ ማስቆጠርያ አማራጭ የያዘ አቀራረብ የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ ግን ጥንካሬውን ማስቀጠል አልቻለም፤ ይህ ጠንካራ ጎናቸውም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች የመመለስ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

በወልዋሎ በኩል ነጋሲ ገብረኢየሱስ፣ ሔኖክ ገብረእግዚአብሔር ፣ ስምዖን ማሩ እና ስምዖን ተኽለ አሁንም ጉዳት ላይ በመሆናቸው በነገው ጨዋታ አይሰለፉም። በመቻል በኩል ደግሞ የሦስት ጨዋታዎች ቅጣት የተጣለበት ሽመልስ በቀለ አይሰለፍም።

በፕሪምየር ሊጉ አራት ጊዜ የተገናኙት ሁለቱም ክለቦች እኩል ሁለት ጊዜ ተሸናንፈዋል፤ በጨዋታዎቹም ሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።

አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በታሪክ በአማካይ 2.3 ግቦች በጨዋታ የተመዘገበበት እና አዝናኝ እና ክፍት ጨዋታ የሚበዛበት የሁለቱም ቡድኖች ግንኙነት ዘንድሮም ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ካከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች የሰበሰበሱት በአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት ጉልህ የሚባል ለውጥ ካሳዩ ቡድኖች ይጠቀሳሉ። በመጨረሻው ሳምንት ከዐፄዎቹ ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በጨዋታው መልካም አጀማመር ማድረግ ቢችልም አድናን ረሻድ በሁለት ቢጫ፤ በቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት መገደዱ በአጨዋወቱ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮበት ነበር። ሆኖም ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ያሳየው ጥንካሬ እና የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች የመጠቀም አቅሙ በአወንታ የሚጠቀስለት ጎኑ ነበር። በነገው ጨዋታ ግን በመልሶ ማጥቃቶች እና ፈጣን ሽግግሮች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገረውን ሀዋሳ ከተማ እንደመግጠማቸው የባለፈውን ሳምንት የመከላከል ጥንካሬ ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ የፊት መስመር ጥምረት ለሀዋሳ ተከላካዮች ፈተና መሆኑ አይቀሬ ነው።

ሁለት ድል፣ አንድ ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ሰባት ነጥቦች የሰበሰቡት ኃይቆቹ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ኃይቆቹ ኡሁንም ውጤታማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እንዳላቸው በማስመስከር ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ነብሮቹ ላይ ድል ባስመዘገበበት ጨዋታ በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብልጫ ቢወሰድበትም በመልሶ ማጥቃት የፈጠራቸውን የግብ ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም ረገድ የነበረው ብልጫ ጨዋታውን እንዲያሸንፍ ረድቶታል። በነገው ጨዋታ ግን በመጨረሻው መርሐግብር  ተጋላጭ የነበረው እና በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ለማስተናገድ የተገደደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ለውጦች ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ያሳየው እና በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረውን ቡድን መግጠሙም ለውጦች አድርጎ እንዲገባ የሚያስገድደው ሌላ ምክንያት ነው።

በአዳማ ከተማ በኩል ዳንኤል ደምሱ ከጉዳት መልስ ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። አድናን ረሻድም በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ሀዋሳ ከተማዎች ከጉዳትም ሆነ  ከቅጣይ ነፃ የሆነውን ስብስብ ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ፤ ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት መሰለፍ ያልቻለው  ቢኒያም በላይም ከጉዳት ተመልሷል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ45 ጊዜያት ያህል ተገናኝተው ሀዋሳ 19 አዳማ ደግሞ 14 ጊዜ ሲያሸንፉ በ12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ጎል በሚበረክትበት የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ሀዋሳ ከተማ 52፣ አዳማ ከተማ 53 ጎሎችን አስቆጥረዋል።