ሪፖርት | ነቢል ኑሪ አዳማን ባለድል አድርጓል

በምሽቱ መርሃግብር ነቢል ኑሪ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች አዳማ ሀዋሳን ረቷል።
አዳማ ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ከፋሲል ከነማ አቻ ከተለያየው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አድናን ረሻድን አስወጥተው በኤልያስ ለገሰ ሲተኩ በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማዎች ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ተባረክ ሄፋሞን ከጉዳት በተመለሰው ቢኒያም በላይ ተክተው ቀርበዋል።

በጨዋታው ጥሩ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ገና በማለዳ ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ በ7ኛው ደቂቃ ነቢል ኑሪ ከቀኝ መስመር የተሻማችን ኳስ በግንባር በመግጨት አዳማ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።

በንፅፅር አዳማ ከተማዎች በቀኝ መስመራቸው በኩል በሚያደርጓቸው የማጥቃት ጥረቶች የበላይ በነበሩበት አጋማሽ ሀዋሳዎች በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጉበት ነበር።

በአጋማሹ 30ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች አቻ ለመሆን እጅጉን ቀርበው ነበር ፤ ዓሊ ሱሌይማን ያደረገውን ሙከራ ዳግም ተፈራ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት እንዲሁም የተለሰችውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ሞክሯት የአዳማ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ተረባርበው ያዳኗት ኳስ አስቆጭ ነበረች።

ቀደም ሲል የታፈሰ ሰለሞን ሙከራን ለማዳን ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ዳግም ተፈራ በ42ኛው ደቂቃ ላይ በናትናኤል ተፈራ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

በ44ኛው ደቂቃ ቢኒያም አይተን ከግራ የሳጥን ጠርዝ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ በሩቁ ቋሚ የነበረው ነቢል ኑሪ በቀላሉ ኳስን በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።

በቀሪው የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች በሦሰት አጋጣሚዎች አደገኛ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ተፈራ የሚቀመስ አልሆነም።

የአዳማ ከተማ ፍፁም የበላይነት በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዳማ ከተማ ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል በመገኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር ፤ በተለይ በ65ኛው ደቂቃ ቢኒያም አይተን ከሰዒድ ሀብታሙ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ እጅግ አስቆጭዋ አጋጣሚ ነበረች።
በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ሀዋሳ ከተማዎች በተወሰነ መልኩ የጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ አዳማ አጋማሽ መግፋት ቢችሉም ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው በአዳማዎች የ2-0 የበላይነት ተፈፅሟል።