በነገው ዕለት የሚደረጉ የሊጉ የአምስተኛ ሳምንት ሦስት መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎችን በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ
ረፋድ ላይ አዞዎቹን ከጣና ሞገዶቹ የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም በተመለሱበት ዓመት የውጤት መንገዱን እስካሁን ያላገኙት አርባምንጭ ከተማዎች ነገ ረፋድ ላይ ከናፈቃቸው ሦስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት ከባህርዳር ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ባደረጓቸ ሦስት የሊግ መርሃግብሮች በሁለቱ ሽንፈት ያስተናገዱት እና አንድ የአቻ ውጤትን አስመዝግበው በደረጃ ሰንጠረዡ አስራ ሰባተኛ ላይ የሚገኘው የአሰልጣኝ በረከት ደሙው ቡድን በነገው ጨዋታ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል ፤ ይሁን እንጂ ቡድኑ መሐል ላይ የእንዳልካቸው እና ይሁን እንዳሻውን የመሐል ሜዳ ጥምረት በይበልጥ ከመስመር ተጫዋቾች ጋር በማገናኘት ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ለመጫወት ሲጥር ቢስተዋልም ቡድኑ በሳጥን ውስጥ የመጨረሻ ኳስ አጠቃቀሙ ላይ ግን ደካማ እንደነበር ካለፉት ጨዋታዎች ተነስተን መናገር ይቻላል።
ቡድኑ የተሻለውን ባህርዳር ከተማን እንደመግጠሙ ነጠ በመከላከል ሆነ በማጥቃቱ ራሱን አሳድጎ መቅረብ ይኖርበታል።
በአሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው እየተመሩ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ድል እና ሁለት ሽንፈትን አስመዝግበው በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ ነገ ፀሀያማ በሆነው የድሬዳዋ ዓየር ከሦስት ነጥብ ፈላጊዎቹ አዞዎቹ ቀላል የማይባል ፉክክር ማስተናገዳቸው ሲጠበቅ ቡድኑ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ አልያም ቸርነት ከግራ እየተነሳ በግሉ በሚደረጋቸው እንቅስቃሴዎችን ለማጥቃት የሚጠቀመው ቡድኑ ይበልጥ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት ጥረት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
ቡድኑ ባደረጋቸው በሊጉ እስካሁን ያስቆጠረው የግብ መጠን ሦስት ብቻ መሆኑ የማስቆጠር አቅማቸው ላይ ከፍተኛ የቤት ስራን እንዳለባቸው አመላካች ነው።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል በመጀመሪያው የሊግ ጨዋታ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ተከላካዩ አበበ ጥላሁን በቅጣት ሳሙኤል አስፈሪ ደግሞ በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል። ባህርዳር ከተማዎች በበኩላቸው ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነው ስብሰባቸውን ይዘው ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ ለአምስተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ሁለት ጊዜ ባህርዳር ከተማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል ሁለቱም ዕኩል ሦስት ሦስት ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ መድን
ሁለቱን የመዲናይዕቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የ10 ሰዓት መርሃግብር ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቅ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች መጨረሻ ጨዋታቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ያስመዘገቡትን ድል ለማስቀጠል በተሻለ የአሸናፊነት ስነ ልቦናን ይዘው በሚቀርቡበት የነገው ጨዋታ በተቃራኒ የመጀመሪያ ድላቸውን እየፈለጉ የሚገኙትን ኢትዮጵያ መድኖች ይገጥማሉ።
በሁለት ጨዋታ አሸንፎ በሁለት የተሸነፈው እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ካለፈው የጨዋታ አቀራረባቸው አኳያ የኋላ መስመራቸው ላይ ማስተካከያን አድርገው እንደሚገቡ ይጠበቃል ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3ለ2 ባሸነፉበት ጨዋታ በመስመሮች በኩል በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ስልነታቸውን ያስመለከቱን ፈረሰኞቹ ጎሎች ከማስቆጠራቸው ባሻገር በቀላሉ ግብ የማስተናገዳቸው ጉዳይ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን የሚያስደስት አይሆንም።
ወጥ የሆነ የጨዋታ መንገድን እስከ አሁን ማሳየት ያልቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው በአንድ ጨዋታ ሽንፈት በቀሩት ሁለት ጨዋታዎች በተመዘገቡ የአቻ ውጤቶች ሁለት ነጥብን ብቻ ይዘው አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ቡድናቸው በብዙ ረገድ መሻሻሎችን ይሻል።
እንደ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ ገለፃ በተደጋጋሚ የዝግጅት ጊዜ ማነስ እና ለብሔራዊ ቡድን በሚያመሩበት ወቅት ቡድኑ ላይ ክፍተቶች ሲታዩ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲገልፁ የነበረ ሲሆን አሰልጣኙ ከዋልያዎቹ ጋር ያላቸው ቆይታ መጠናቀቁ በአንድ ልብ ቡድናቸውን ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚረዳቸው ይጠበቃል።
ቡድኑ መሀል ሜዳው በአብዛኛው ከመሀል ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች ለመጫወት የሚያደርገውን አጨዋወት ነገ የበለጠ አሳድጎ እንደሚቀርብ ቢጠበቅም በመስመር መከላከል ይታይበት የነበረውን ክፍተት ግን መዝጋት ካልቻለ በቅዱስ ጊዮርጊሶች የመስመር ማጥቃት ጫና ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በረከት ወልዴ ብቸኛው ቡድኑ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች ሲሆን መድኖች ግን ሚሊዮን ሠለሞን እና ዋንጫ ቱትን በቅጣት አያገኙም ፣ መሐመድ አበራ እና ሐቢብ ከማል ግን ከጉዳት ተመልሰዋል።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 27 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 19 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 50 ጎሎች ፣ 3 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 15 ግቦችን አስቆጥረው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና
ሁለቱን ቡናማዎች የሚያገናኘው የነገ ምሽቱ ተጠባቂ መርሀግብር የመጨረሻ ትኩረታችን ነው።
በሩዱዋ ደርቢ በሀዋሳ ከተማ ከተረቱ በኋላ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች እየነቁ የመጡት ሲዳማዎች ቀጣይ ያደረጓቸውን ሦስቱንም ጨዋታዎች በድል ተወጥተው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በዘጠኝ ነጥቦች ሲቀመጡ ነገም ካቆሙበት ለመቀጠል ከአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬው ቡድን ጠንከር ያለ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
የሊጉ መሪ ይሁኑ እንጂ በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አራት ግቦችን ብቻ እስከ አሁን ማሳረፍ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ይበልጥ በተሻጋሪ እና በፈጣን ሽግግር አጨዋወታቸው አራተኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በሁሉም የሜዳ ክፍል ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን ይዞ የሚገኘው ቡድኑ ምን አልባትም ካለፉት ተከታታይ ጨዋታዎቹ የአጨዋታ መንገዱ ላይ ለውጥ ባያደርጉም ኢትዮጵያ ቡናን እንደመግጠማቸው በንክኪዎች በቶሎ ሳጥን ሲደርሱ በሚስተዋሉት የመዲናይቱ ክለብ ግን በብርቱ መፈተናቸው አይቀርም።
የወድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድላቸውን ለማሳካት የሚያልሙት ኢትዮጵያ ቡናዎቹ ለኳስ ቁጥጥር ይበልጥ ትኩረት በመስጠት የሚንቀሳቀሱበትን አቀራረብ ይበልጥ በማሳደግ ነገ ባለፈው ሳምንት ካስተናገዱት ሽንፈት ለማገገም ይጫወታሉ ፣ ቡድኑ በቅብብሎች ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ባይቸገርም በቀላሉ ግቦች የማስተናገዱ ነገር ግን እርምትን ይሻል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ራምኬል ጀምስ በቅጣት በፍቃዱ ዓለማየሁ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በሲዳማ ቡና በኩል ጉዳትም ሆነ ቅጣት ሳይኖር ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 28 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 10 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን በ10 ጨዋታ አቻ ተለያይተው 8 ጨዋታ ሲዳማ ቡና አሸንፏል። ኢትዮጵያ ቡና 37 ሲዳማ ቡና 28 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።