ሪፖርት | አዞዎቹ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገዋል

አርባምንጭ ከተማ በፍቅር ግዛው ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ባህርዳር ከተማን 1ለ0 የዓመቱን የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል።
በሦስተኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት አርባምንጮች ኢድሪስ ኦጎዶጆን በፋሪስ ዕላዊ ፣ አህብዋ ብሪያንን በአሸናፊ ተገኝ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በአንፃሩ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ የተረቱት ባህርዳሮች በበኩላቸው ባደረጓቸው የአራት ለውጦች ወንድሜነህ ደረጀ ፣ መሳይ አገኘሁ ፣ ፍቅረሚካኤል አለሙ እና ሙጂብ ቃሲምን በፍፁም ፍትሕአለሙ ፣ ፀጋዬ አበራ ፣ ጂሮም ፊሊፕ እና አቤል ማሙሽ ተክተው ቀርበዋል።

እጅግ ከረር ባለው የድሬዳዋ ፀሀያማ የአየር ንብረት መደረጉን በጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በይበልጥ መሐል ሜዳ ላይ በቁጥር በዝተው ለመጫወት የሞከሩበት ነበር።

ከአማካይ ክፍል በሚነሱ ኳሶችን አህመድ ሁሴን መፈልግ የጀመሩት አርባምንጮች ጥረታቸው ብዙም ፍሬያማ አልነበረም።

በአንፃሩ አጀማመራቸውን ዝግ ያለ የነበሩት ባህር ዳሮች በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ወደ አርባምንጭ ሳጥን ለመድረስ ያደረጉት ጥረት ውጤት ሳያስገኝም አጋማሹ ያለ ግብ ሙከራ ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም ባልተለወጠው ሁለተኛው አጋማሽ የጣናው ሞገድ ኳስን ይበልጥ ለመቆጣጠር የጣሩበት ነበር።

በ58ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሠለሞን የአርባምንጭ ተከላካዮች በአቋቋም የፈጠሩትን ስህተት ተመልክቶ የጣለለትን ኳስ አቤል ማሙሽ ነፃ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኛትን መልካም አጋጣሚ ሳይጠቀማት ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ቀጥተኝነትን ጨምረው የቀረቡት አዞዎቹ በ75ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ በፍቅር ግዛው ከመረብ አሳርፎ አዞዎቹን መሪ አድርጓል።

በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ወደ አቻነት ለመምጣት ባህርዳሮች ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ የ1ለዐ አሸናፊነት ተደምድሟል።