ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሙገር ስሚንቶ

በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙገር ሲሚንቶን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ በጨዋታው የታዩ ታክቲካዊ ጉዳዮችን ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተመልክቷቸዋል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከወገብ በታች ተቀመጠው ሙገር ሲሚንቶ ከአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጫውቷል፡፡ እንግዳው ቡድን በሁለት አጥቂዎች መጫወቱን ቢቀጥልም ጎሎችን ማስቆጠር ግን ተስኗቸዋል፡፡ 4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርም የዘንድሮ የቡድን ተመራጭ የአጨዋወት ሲስተም መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ፈረሰኞቹ ደግሞ 4-3-3 ፎርሜሽንን ባብዛኛው የጨዋታው ክፍል ጊዜ ተተቅመዋል፡፡ (ተስፋዬ አለባቸው በመጨረሻ 81 ኛው ደቂቃ ላይ) ፋሲካ አስፋውን ተክቶ ወደ ሜዳ እስከገባበት ሰዓት ድረስም 4-3-3ን ሲተገብሩ ተስተውለዋል፡፡ ከዛ በኋላ 4-2-3-1ን ተጫውተዋል፡፡ ምስል (1)

Giorgis 2-0 Mugher (1)
የሙገሮች የቀኝ መስመር ክፍተት

የአሰልጣኝ ግርማ ሀበተዮሃንስ ቡድን በወጣቶች ተዋቀረና በታክቲክ አተገባበር የተሻሉ ተጫዋቾችን ቢይዝም ለተጋጣሚ ቡድኖች የሚሰጠው የመጫወቻ ክፍተትም ለተደጋጋሚ ሽንፈቶች እያጋለጠው ይገኛል፡፡ የመስመር ተከላካዮች በመጀመሪያው አጋማሽ የቡድናቸው የማጥቃት አጨዋወት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ አልነበረም፡፡ የመስመር አማካዮቹም ከኋላቸው ካሉት የቡድን አጋሮቻቸው በተጋጣሚያቸው ሜዳ የላይኛው ክፍል (Higher –up the pitch) የማጥቃት ድጋፍ ሲያገኙ አልታዩም፡፡ ይህም ሙገር በ Flat back 4 (ተከላካዮች በሙሉ በአንድ መስመር ላይ ሲሆኑ የሚፈጠር የመከላከል ቅርፅ) ከመጫወቱ ጋር ተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ መስመር ተከላካዮቹ ለመሃል ተከላካዮች ቀርበው መጫወታቸው በሁለቱም መስመሮች ያሉት (Chanel) በመስመር ተከላካይና በመሃል ተከላካይ መካከል ያለው ክፍተት እንዲጠብ ቢያደርግም የሜዳውን የጎንዮሽ ክፍል በተጋጣሚ ቡድን አስፍተው የሚጫወቱ አጥቂዎችና አማካዮች ተጋላጭ እንዲሆኑና ጫና እንዲፈጥርባቸው አድርጓል፡፡ ሁለቱ የመሃል ሜዳ አማካዮም በጨዋታው እናቅስቃሴ ይበልጥ ለተከላካዮቻቸው ቀርበው የነበረ መሆኑ የመስመር አማካዮቹ ወደ ኋላ ተስበው ወደ መሃለኛው የሜዳ ክፍል እንዲገቡ የገፋፋቸውን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ (ኳስን ፍለጋ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡) በተለይ የቡድኑ የቀኝ መስመር እጅግ ክፍት እንደነበር ማስተዋል ይቻላል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የጎል ሙከራዎቻቸው በሙሉ ከዚህኛው መስመር መገኘቱ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ፍፁም ምን ያህልና በተለይም ዘካርያስ በዚህኛው ክፍል እንደፈለጉ ሲንቀሳቀሱ የታዩትም ለዚህ ይመስላል፡፡ ምስል (2)

Giorgis 2-0 Mugher (2)
የጊዮርጊሶች የመሃል ሜዳ የቁጥር የበላየነት እና ጠቀሜታው

ቻምፒዮኖቹ መሃል ሜዳቸው በጥሩ አማካዮች የተዋቀረ ነው፡፡ 3ቱም ተጫዎቾች (በመሃል ሜዳ የተሰለፉት) የቴክኒክ ክህሎት ፣የታክቲክ አተገባበር እና ቦታን ጠብቆ መጫወት ላይ ያላቸው ብቃት የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ወጣቱ ናትናኤል የትሪያንግሉን ጫፍ በብቃት ሲመራ በግራው ምንያህል በቀኝ ደግሞ ፋሲካ መሃል ሜዳውን ተቆጣጥረውት አምሽተዋል፡፡ በከፍተኛ ተጭኖ የመጫወት ዘዴም (pressing) የተጋጣሚያቸው አማካዮች ላይ የቁጥር የበላይነት ሲያሳዩ ነበር፡፡ ሙገር በመሃል ሁለት የአማካይ ተከላካዮች ማሰለፉ ፋሲካ ፤ ናትናኤል እና ምንያህል ከፊታቸው ሰፊ ክፍተትን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ፍፁም ፤ አዳነ እና በሃይሉ (ቱሳ) የተጋጣሚያቸው ተከላካዮች ላይ ጫና በመፍጠር (press በማድረግ) ጥሩ ሲንቀሳቀሱ አምሽተዋል፡፡ በማጥቃት አጨዋወት ላይ ምንያህልና ፋሲካ ወደ መሃለኛው የሜዳ ክፍል ሲገቡ ዘካርያስና ቢያድግልኝ የመስመር የማጥቃት አጨዋወት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲያግዟቸው ነበር፡፡ ወደ መስመሩ ተጠግትውም የመቀባበያ አማራጮችን እና የማጥቃት ማዕዘናትን ሲፈጥሩላቸው ነበር፡፡ ይህም ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን እንዲያደርጉ አግዟቸዋል፡፡ በ41ኛወ ደቂቃ ላይ ዘካርያስ በግራ መስመር አዳነ ላስቆጠራት ኳስ ያሻገራት ኳስም ቡድኑ የመስመር ተከላካዮቹን በላይኛው የሜዳ ክፍል ባብዛኛው እንዲገኙ ከማድረጉ ጋር በተያያዘ ይመስላል፡፡ ደጉና ሰላዲንም overlap የሚያደርጉ ፉልባኮችን ቦታ ሲሸፍኑ ናቲ ወደ ኋላ እየተሳበ የመሃሉን ክፍተት በመሸፈን ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እንዳይጋለጥ የበኩሉን ሚና ሲወጣ ነበር፡፡ ምስል (3)

Giorgis 2-0 Mugher (3)
ከዕረፍት መልስ

በሁለተኛ አጋማሽ አሰልጣኝ ግርማ በቡድናቸው አጨዋወት ላይ መጠነኛ ለውጥ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ የመስመር ተከላካዮቻቸው የበለጠ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡ አንድ ተጫዋች በጨዋታ ሶስት ሚናዎችን የወሰደበት አጋጣሚም የተፈጠረው በዚህኛው አጋማሽ ነው፡፡ ቡድኑ የግራ መስመር አማካዩ ሱራፌል ጌታቸው(8)ን አስወጥቶ አጥቂው ኤፍሬም ቀሬ(7)ን ሲያስገባ ከሙገር ሁለቱ አጥቂዎች አንዱ የነበረው አዲሱ አላሮ (11) ከአጥቂነቱ ተነስቶ የግራ መስመር አማካይ ሆነ፡፡ በሌላ ቅያሪም ክንዳለም ፍቃዱ (13) ወጥቶ 19 ቁጥር ሲገባ ይሄው ተጫዋች (አዲሱ) የግራ መስመር ተከላካይነት ሚናን መወጣት ጀመረ፡፡ በእነኚህና መሰል የተጫዋችና የቦታ ለውጦች የተነሳም ሙገር መጠነኛ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ የጊዮርጊሶች ፋልባኮች ጥለውት የሚሄዱትን ቦታ ለመጠቀምም ሲጥሩ ታይተዋል፡፡ ነገር ግን የተጫዋቾቹ የኳስ ቅብብሎሽ ትክክለኛነት ደካማ ነበር፡፡ የታሰበላቸውን ቦታዎችና ተጫዋቾች ያማከላ ምጣኔም ይጎላቸው ነበር፡፡ በተቃራኒው ጊዮርጊሶች በናትናኤልና በፋሲካ ሲያደርጓቸው የነበሩት ረጃጅም ኳሶች ምጣኔ ትክክለኛነት የሚያስገርም ነበር፡፡ ሙገር ላይ ጫናን የሚፈጥሩ ሙከራዎችም ከነዚህ በረጅሙ ከሚላኩ ኳሶች ተገኙ ነበሩ፡፡ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ያስቆጠራት ጎልም የዚህ ማሳያ ነበርች፡፡ ለጎሏ መገኘት የቱሳ ረጅም ኳስ (ከመስመር የተሻገረ) ምጣኔ እና እይታ አይነተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ቡድኑም በዚሁ ጨዋታውን አሸንፎ ሊወጣ ችሏል፡፡ (ምስል 4)

Giorgis 2-0 Mugher (4)

ያጋሩ