ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ንግድ ባንክ ላይ ድል ከተቀዳጀው ቋሚ አሰላለፍ በረከት ወልዴን በፍሪምፖንግ ክዋሜ ተክተው ሲገቡ መድኖች በበኩላቸው በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገደ ቋሚ ስብስብ ሀይደር ሸረፋን በመስፍን ዋሼ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ የታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥቂት ግን ደግሞ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በተለይም በአጋማሹ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ የነበሩት መድኖች ጋቶች ፓኖም ከርቀት አክርሮ ካደረጋት የመጀመርያ ሙከራ በኋላ በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ሁለት ለግብ እጅግ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል።

አጥቂው ከመሀል ሜዳ የተሻገረችለትን ኳስ በአግባቡ ካመቻቸ በኋላ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት እና በተመሳሳይ መንገድ ከረመዳን የሱፍ በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ሞክሮ ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ በአጋማሹ ከታዩ ሙከራዎች የተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። መድኖች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በመስፍን ዋሼ አማካኝነት ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። አማካዩ በረከት ካሌብ ከመስመር ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ መቷት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ኳስም በመድን በኩል የተደረገች የአጋማሹ የመጨረሻ ሙከራ ነበረች።

በአጋማሹ የግብ ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ደካማ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በአብርሀም ጌታቸው አማካኝነት ከቅጣት ምት ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በፍፁም ጥላሁን እና አማኑኤል ኤርቦ ካደረጓቸው ተጨማሪ ሙከራዎች ሌላ የቀረበ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

ከመጀመርያው አጋማሽ ጋር ተቀራራቢ ፉክክር በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች
ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር።
አቡበከር ሳኒ ተቀይሮ የገባው አሸብር ደረጄ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ባደረገው ሙከራ የጀመሩት መድኖች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ዳዊት ተፈራ አሻምቷት አብዲሳ ጀማል በግንባሩ ገጭቶ ባሕሩ ነጋሽ ካዳናት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ዘግይተው ተስፋ ሰጪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በአጋማሹ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሙከራዎችን አድርገዋል። አዲስ ፈራሚው መሐመድ ኮኔ ከፍፁም ጥላሁን የተሻገረችውን ኳስ አፈትልኮ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አቡበከር ኑራ የተቆጣጠራት ኳስ እና ፍፁም ጥላሁን በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎችም የሚጠቀሱ ናቸው። ጨዋታው ባዶ ለባዶ መጠናቀቁ ተከትሎም መድኖች በውድድር ዓመቱ ሦስተኛ የአቻ ውጤታቸውን ሲያስመዘግቡ ፈረሰኞቹ የውድድር ዓመቱን ነጥባቸውን 7 አድርሰዋል።