ሪፖርት | ሲዳማ ቡና በድል ጉዞው ቀጥሏል

ሲዳማ ቡናዎች በሁለቱም አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ0 አሸንፈው የሊግ መሪነታቸውን አጠናክረዋል።

የሊጉን የላይኛውን ጫፍ ተቆናጠው የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 ከረታው ቡድናቸው የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪን ሲያደርጉ ጊት ጋትኩት ፣ ኢማኑኤል ላርዬ እና ይገዙ ቦጋለ ቦታ ላይ ያሬድ ባየህ ፣ ብርሃኑ በቀለ እና ሬድዋን ናስር ተተክተው በቋሚነት ሲገቡ በወላይታ ድቻ ከመምራት ተነስተው ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ቅጣት ባስተናገደው ራምኬል ጀምስ ገዛኸኝ ደሳለኝን ፣ በበፍቃዱ ዓለማየሁ ረጂብ ሚፍታህን እንዲሁም ይታገሱ ታሪኩን በኤርሚያስ ሹምበዛ ለውጠው ቀርበዋል።

የኃይል መጠኑ ከፍ ባለ ዝናብ እየታጀበ በፌዴራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ መሪነት በጀመረው የምሽቱ ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚመስል አቀራረብን በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ብናስተውልም በሒደት በፈጣን ሽግግር ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የመጡት ሲዳማ ቡናዎች ብልጫውን መያዝ ችለዋል። ከራሳቸው ሜዳ ከሚያደርጓቸው ቅብብሎች በኋላ ፈጥነው ሦስተኛው ሜዳ ላይ በቶሎ የሚደርሱት ሲዳማዎች በተለይ ከመስመር በሚነሱበት ጊዜ በቀላሉ የተጋጣሚያቸውን መከላከል ሲፈትኑ ታይተዋል። በ10ኛው ደቂቃ ከዚሁ የጨዋታ መንገድ ሀብታሙ አመቻችቶ በሰጠውን እና መስፍን ታፈሠ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ ኢብራሂም ዳላንድ በመከተበት አደገኛ ሙከራን ሰንዝረዋል።

ተጋጣሚያቸው የሚፈጥሩላቸውን የቅብብል ስህተቶች ከመጠቀም ባለፈ የተወሰነ የመልሶ ማጥቃትን መጫወት ምርጫቸው ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተጋጣሚያቸው የተፈጠረባቸውን ብልጫ ተከትሎ ራሳቸው በፈጠሩት ስህተት ግብን አስተናግደዋል። 29ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ወልደአማኑኤል የሰጠውን ኳስ ስንታየሁ ለመቀበል ሲቃጣ በዝንጉት ያመለጠው ኳስን ከጀርባ የነበረው ሀብታሙ ፈጥኖ ተቆጣጥሮ ያቀበለውን አበባየሁ ሀጂሶ አግኝቶ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ብዙም የግብ አጋጣሚዎች አይፈጠሩበት እንጂ ሲዳማ ቡና በይበልጥ ብልጫውን እየያዘ በመጣበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎቹ ከቆሙ ኳሶች ግብን ለማስቆጠር በድግግሞሽ ጥቃቶችን ቢያደርጉም ኢብራሂም ዳላንድን አልፎ የሚቆጠር ኳስ ባለ መኖሩ አጋማሹ 1ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ መጠነኛ አጀማመርን ካደረጉ በኋላ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ መሆን የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች አቀራረባቸውን ከፍ አድርገው ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም መንቀሳቀስን መርጠው ታይተዋል። በእንቅስቃሴ ረገድ ተሻሽለው ቢቀርቡም ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች መፍጠር ያቃታቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በመከላከሉ ያሳዩት ወረድ ያለ ሽፋን ሁለተኛ ጎልን በተመሳሳይ የተጫዋች ስህተት እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል።

63ኛው ደቂቃ ላይ ከራስ ሜዳ የግብ ዘቡ ኢብራሂም ዳላንድ ለማራቅ የመታት ኳስን ያገኘው ያሬድ ባየህ ወደ ጎል ሲሞክር የግቡን አግዳሚ ብረት ገጭታ ስትመለስ ሀብታሙ ታደሠ በቀላሉ ወደ ግብ ለውጧት ውጤቱ ወደ 2ለ0 ተለውጧል። በእንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ በመጣው የመጨረሻዎቹ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚመስል ፉክክር የነበረው ቢመስልም አሁንም የጎል አጋጣሚዎችን ላቅ ባለ ደረጃ የፈጠሩት ሲዳማ ቡናዎች ናቸው።

ሀብታሙ ታደሠ በአንድ ለአንድ ግንኙነት በኢብራሂም ዳላንድ የዳነበት እንዲሁም ደግሞ ፍቅረየሱስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ኢብራሂም ዳግም የተቆጣጠራት 75ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሀብታሙ ታደሠ ሦስተኛ ግብ አደረገው ተብሎ ሲጠበቅ ለኢብራሂም ያሳቀፈው አጋጣሚ ምንአልባትም የሲዳማን መሪነት ሊያሰፉ የሚችሉ ዕድሎች ነበሩ። በመጨረሻዎቹ የጭማሪ ደቂቃዎች ዘግይተው ወደ ጨዋታው ለመግባት የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት አላስቻላቸውም ፣ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንድ ሲቀር የሲዳማ ቡናው ማይክል ኪፕሩቪ ሦስተኛ ልትሆን የምትችል አጋጣሚ በግቡ አግዳሚ ከተመለሠችበት በኋላ 2ለ0 በሆነ ውጤት በሲዳማ አሸናፊነት ተቋጭቷል። ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና የሊግ መሪነት ነጥቡን አስራ ሁለት አድርሷል።