ሪፖርት| ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀድያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

ጥቂት የግብ ሙከራ በታየበት የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ባህርዳር ከተማን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታው ሲገቡ ሀድያ ሆሳዕዎች ግን ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ሳማኪ ሚካኤል፣ ከድር ኩሉባሊ፣ ፀጋአብ ግዛው፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ሳሙኤል ዮሐንስ በያሬድ በቀለ፣ ቃልአብ ውብሸት፣ በረከት ወልደዮሐንስ፣ መለሰ ሚሻሞ እና ፀጋአብ ግዛው ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከትናንት በስትያ ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ በተደረገ የህሊና ፀሎት የጀመረውና በእንቅስቃሴ ረገድ ማራኪ ያልነበረው የመጀመርያው አጋማሽ እጅግ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ብያደርጉም ሙከራዎች በማድረግ በአንፃራዊነት የተሻለ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በአጋማሹ በእዮብ አለማዮህ እና በረከት ወልደዮሐንስ ዒለማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አድርገዋል።

በረከት ከቅጣት ምት በቀጥታ መቷት ግብ ጠባዊው ወደ ውጭ ያወጣት እና ከሳጥኑ የግራ ክፍል እዮብ ከብሩክ የተቀበላትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ወጥቶ ያዳናት ኳስም የተሻለ ለግብ የቀረበች ሙከረ ነበረች። በአጋማሹ ከግብ ጠባቂ ጀምረው ኳስ ለመመስረት ጥረት ያደረጉት ኤሌክትሪኮችም የተጋጣሚየቸው ጫና ፈጥሮ የመጫወት ሂደት አልፈው ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

የሀድያ ሆሳዕናዎች ብልጫ በታየበት እና ጥቂት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙክራዎች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ነብሮቹ በቁጥርም ይሁን በጥራት የተሻሉ የግብ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር። ከነዚህም እዮብ አለማየሁ እና ብሩክ በየነ ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ፤ በተለይም ብሩክ በየነ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ተመስገን ብርሀኑ ከመስመር አሻግሯት አክሮባቲክ በሆነ መንገድ የሞከራት ኳስ ነብሮቹን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው ካስገቡ በኋላ የተሻለ ጫና ፈጥረው ሙከራዎች ማድረግ የቻሉት ነብሮቹ በበየነ ባንጃው አማካኝነትም እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ተጫዋቹ ከመስመር ተሻምታ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች የጨረፏት ኳስ አክርሮ በመምታት የግቡ አግዳሚ የመለሳት ኳስም የጨዋታው ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች። በጨዋታው በመከላከሉ ላይ ካሳዩት ጥንካሬ ውጭ አመርቂ የሚባል የማጥቃት አጨዋወት ያልነበራቸው ኤሌክትሪኮችም በሽመክት ጉግሳ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፤ ተጫዋቹ ከቅጣት ምት በቀጥታ መቷት ኢድሪሱ አብዱላሂ ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራም ብቸኛዋ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።


ጨዋታው በአቻ መጠናቀቁን ተከትሎ ኤሌክትሪክ የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ የአቻ ውጤቱን ስያስመዘግብ ሀድያ ሆሳዕና ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት መልስ አንድ ነጥብ አሳክቷል።