ሪፖርት | የጦና ንቦች ተከታታይ ድል አሳክተዋል

በሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ የጦና ንቦች ስሑል ሽረን በያሬድ ዳርዛ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።

ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን ከረታበት ቋሚ አሰላለፍ ተስፋዬ መላኩን እና ብዙአየሁ ሰይፉን በኬኔዲ ከበደ እና አብነት ደምሴ ተከተው ሲገቡ ስሑል ሽረዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ አሰላለፍ ክፍሎም ገብረሕይወትን እና አሌክስ ኪታታን በማሳረፍ መሐመድ አብዱላጢፍ እና ብርሃኑ አዳሙን በምትካቸው በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተመጣጣኝ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ስሑል ሽረዎች ኳስ ተቆጣጠረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ወላይታ ድቻዎች በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል በተደጋጋሚ ቢደርሱም ሁነኛ ሙከራ አላደረጉም።

ስሑል ሸረ በአንፃራዊነት በኳስ ንክኪ ብልጫ በወሰደበት አጋማሽ ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም ሆነ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ወደ ግብ ክልል ቢገቡም ጠንከር ያለ ሙከራ አላደረጉም። እንዲሁም ከኋላ ጀምረው ኳስ መስርተው መጫወት ቢችሉም ወደ ጦና ንቦች ግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት የወላይታ ድቻ ተከላካዮች በቀላሉ በማበላሸት ጠንካራ መከላከል አስመልክተዋል።

ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በሰላሳዎች ደቂቃ መጨረሻ አካባቢ አከታትለው ያገኙትን የቆመ ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ቀጥታ ወደ ግብ ቢመቱም የስሑል ሽረው ግብ ጠባቂ ሞይስ ፓዎቲ በቀላሉ ተቆጣጥሯቸዋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት የስሑል ሽረ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው ቢመታም ኳሷ ከፍ ብላበት አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው የገቡት ወላይታ ድቻዎች ጫን ብለው በመጫወት መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ለማስቆጠር ከእረፍት መልስ ዘጠኝ ደቂቃ ጠብቀው በ54ኛው ደቂቃ ኳስና መረብ አገናኝተዋል። የስሑል ሽረ ተከላካዮች ግብ ክልል አካባቢ ኳስ ለመቀባበል ሲሞክሩ ካርሎስ ዳምጠው ቀምቶ ያለቀ ኳስ ለያሬድ ዳርዛ አቀብሎት ያሬድ ዳርዛ መረብ ላይ አሳርፏታል።

 

የተሻለ የግብ ማግባት ተነሳሽነት የተላበሰው አጋማሹ ከደቂቃ ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማግባት ጥረት ያደረጉበት ነበር። በአንድ ግብ ብቻ ማብቃት ያልፈለጉት የጦና ንቦችም የተጨማሪ ግብ ፍለጋ ሽግሽግ ላይ ሽንፈት ላለመቅመስ ጫና የፈጠሩት የሽረዎች እንቅስቃሴ ታክሎበት ለጨዋታው ግለቱን ጨምሯል። በ85ኛው ደቂቃ ላይ ስሑል ሽረዎች አቻ ለመሆን የተቃረቡበትን ሙከራ በመስመር በኩል ኳስ ይዘው ገብተው ቢያደርጉም የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ ተረባርቦ አድኖባቸዋል። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች እና በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ወላይታ ድቻዎች ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል መጫዎት ውጤታማ ሆኖ ውጤቱን አስጠብቀው ሦስት ነጥብ ከአንድ ግብ ጋር ተቀዳጅተው ተከታታይ ድል አስመዝግበው ጨዋታው ተጠናቋል።